የኦፌኮ ፓርቲ አባል የሆነው ጀዋር ሙሃመድ ከመንግስት ባላስልጣናት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገባ

(ERF) በኦሮምያ ጉዳይ ከአብይ መንግስት ጋር በጋራ እየተመካከር በመስራት ላይ ነን በማለት መግለጫ ሰጥቶ የነበረው የኦሮምያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ የነበረውና በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራውን ኦፌኮን የተቀላቀለው አቶ ጀዋር ሙሃመድ፣ ዶ/ር አብይ እና በዙሪያቸው ካሉ ባለስልጣናት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።

አቶ ጃዋር በምርጫ ቦርድ የዜግነት ጥያቄ የቀረበበት ሆን ተብሎ እሱን ከምርጫው ለማገድ ነው እያለ በመናገር ላይ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አንድ ሴት በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ላይ በቀጥታ በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ ፣ ከነፍጠኛ ብሄር ጋር አትጋቡ፣ የተጋባችሁም ፍቱ ብላ በመናገሯ፣ የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ጣላሁን፣ ድርጊቱን አውግዘው በጣቢያው ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸውን ተከትሎ አቶ ጃዋር በመንግስት ላይ የሚያሰማውን ተቃውሞ አጠናክሯል።

አቶ ጀዋር ተቃውሞውን ያነጣጠረው በጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ በአማካሪያቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ በቃል አቀባዩ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና በምርጫ ቦርድ ሃላፊዋ ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ላይ ነው።

አቶ ጀዋር በእርሱ ላይ የተከፈተው ዘመቻ የኦሮሞን ህዝብ ለማጥቃት የተከፈተ ዘመቻ አድርጎ እንደሚመለከተው ለደጋፊዎቹ በፌስቡክ ገጹ ላይ እየገለጸ ነው።

የኦሮምያ የብልጽግና ፓርቲ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደዓም እንዲሁ በአቶ ጀዋር ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት አጠናክረው ቀጥለዋል። በመጪው ምርጫ በአቶ ጀዋር እና በዶ/ር አብይ ድጋፊዎች መካከል ግጭት ይፈጠራል ተብሎ ተሰግቷል። የኦሮምያ ክልል ሊፈጠሩ የሚችሉትን ግጭቶት ለመቆጣጠር በሚመስል መልኩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የልዩ ሃይል አባላትን አሰልጥኖ በማስመረቅ ላይ ነው።

ፌደራል ፖሊስ ለአቶ ጃዋር ይሰጠው የነበረውን የጥበቃ አገልግሎት አቋርጧል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: