ዶ/ር አብይ አህመድ አዳነች አበቤን ዋና አቃቢ ህግ ላቀ አያሌውን የገቢዎች ሚኒስትር አደረጉ

(ERF)ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የገቢዎች ሚኒስትር የሆኑትንና በስራቸው ከፍተኛ ምስጋና ያተረፉትን ወ/ሮ አዳነች አበቤን የፌደራል ጠ/አቃቤ ህግ አድርገው ሲመርጡ፣ የቀድሞው የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት የነበሩትንና በቅርቡ ከሃላፊነት የተነሱትን አቶ ላቀ አያሊውን ደግሞ በወ/ሮ አዳነች ቦታ ተክተዋቸዋል። እንዲሁም ኮሮና ቫይረስን በመከላከል በኩል ባሳዩት ብቃት የተወደሱት ዶ/ር ልያ ታደሰ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነዋል።

የሶስቱ ባለስልጣናት ሹመት ነገ ሃሙስ በፓርላማ ይጽድቃል።

ወ/ሮ አዳነች የገቢዎች ሚኒስትር ከሆኑ በሁዋላ መስሪያ ቤቱ አዳዲስ ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረጉ እንዲሁም የመንግስትን ገቢ በመጨመር በኩል ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። ይሁን እንጅ ቀደም ብሎ በስራ የሚያውቋቸውን ጓደኞቻቸውን ወደ መስሪያ ቤቱ ሰብስበዋል በሚል ትችት ሲቀርብባቸው ቆይቷል።

አቶ ላቀ አያሌው ከአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ መደረጉ የክልሉን ባለስልጣናት ከሁለት ከፍሎ ቆይቷል። ጠንካራ የመሪነት ችሎታ አላቸው የሚባሉት አቶ ላቀ፣ ወደ ፌደራል የተዛወሩት አማራ ክልልን ለማዳከም ታስቦ ነው በማለት አንዳንድ የአማራ ክልል የፓርላማ አባላት በስብሰባ ወቅት አስተያየት ሰጥተው ነበር። አቶ ላቀ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በአማራ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ ላይ የብ/ጄ አሳምነው ጽጌ ቡድን ከወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ ስማቸው እየተነሳ ሲተቹ ቆይቷል። እርሳቸው ተለይተው በህይወት መትረፋቸው እንደሚጸጽታቸው ሲነገሩ የተሰሙት አቶ ላቀ፣ ከሰኔ 15 በሁዋላ ከባድ የሆነ ህይወት አሳልፈዋል።

እንደ አቶ ላቀ ሁሉ ከስልጣን የተነሱት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጸሃፊ አቶ ዮሃንስ ቧያለው የመለስ አካዳሚ ዳይሬክተር ሆነው ቢሾሙም ፣ ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

የኮሮና ቫይረስን በመከላከል በኩል ባሳዩት ትጋት ምስጋና ያተረፉት ዶ/ር ሊዲያ ታደሰ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነ እንዲሆኑ መመረጣቸው ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ተወስዷል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: