በመጪው ምርጫ ማን የተሻለ የማሸነፍ እድል አለው?

( ERF) በሚቀጥለው ነሃሴ ወር ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ የተለያዩ አገራቀፍና ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ይወዳደራሉ። የእነዚህ ፓርቲዎች እድሎችና ፈተናዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን። እናንተም ማን የተሻለ የማሽነፍ እድል እንዳለው አስተያየት ስጡበት ።

ብልጽግና ፓርቲ

ፓርቲው መንግስታዊ ተቋሙን የያዘ መሆኑ ፣ ከፍተኛ የገንዘብ አቅምና አደረጃጀትም ያለው በመሆኑ ከሌሎች ድርጅቶች በተሻለ የማሸነፍ እድል አለው። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብይ አህመድ ያላቸው ተቀባይነት እንዲሁም መደመር በሚል አስተሳሰብ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርጸው መምጣታቸው በምርጫው ላይ ከፍተኛ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል። ፓርቲው በሴቶች እና በአረጋውያን ላይ የሚሰራው ስራ፣ የሴቶችንና የአረጋውያንን ድጋፍ ለማግኘት ይረዳዋል።የብሄር ፖለቲካ ለአገሪቱ እንደማይጠቅም የሚያስበው የህብረተሰብ ክፍልም ከዶ/ር አብይ ውጭ አገሪቱን የሚመራት ሌላ የተሻለ ሰው አይኖርም በሚል፣ ብልጽግናን ሊመርጥ ይችላል። በአገሪቱ የሚታየው ግጭት ከቀነሰ እንዲሁም ኢኮኖሚው ተሻሽሎ የስራ አጡን ቁጥር የሚቀንሰው ከሆነ ብልጽግና አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበት እድል ዝግ አይደለም።

የብልጽግና ዋና ተቀናቃኞች የብሄር ፖለቲካ አራማጆች ናቸው። በአማራ ክልል ከብጄ/ል አሳምነው ጽጌ የሰኔ 15 ድርጊት ጋር በተያያዘ፣ የዶ/ር አብይ ተቀባይነት መቀነሱ፣ የታገቱ የአማራ ሴት ተማሪዎች ጉዳይና በአጠቃላይ የአማራ ብሄርተኞች ዶ/ር አብይ አህመድን ጸረ አማራ አድርገው ለማሳየት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ብልጽግና በተለይ በአማራ ወጣቶች ዘንድ  የሚኖረውን ተቀባይነት በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስበት እንደሚችል ይገመታል።

በኦሮምያ ክልል ደግሞ የአቶ ለማ መገርሳ ከፖለቲካው ማፈግፈግ፣ ከኦነግና ኦፌኮ ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ እርምጃዎች መጠናከር እንዲሁም የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክና አክቲቪስቶች ዶ/ር አብይ አህመድን የኦሮሞ ስነልቦና የሌላቸው አድርገው ለማሳየት የሚሄዱበት እርቀት፣ ብልጽግና ፓርቲ በኦሮምያ ክልል ከፍተኛ ፈተናዎች ይገጥሙታል። ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ምንም አይነት ድምጽ እንደማያገኝ ፣ ክህወሃት ባህሪ አንጻር ተነስቶ መናገር ይቻላል።

ብልጽግና ፓርቲ የተሻለ ድምጽ ሊያገኝባቸው ይችላል ተብሎ ከሚገመቱ አካባቢዎች መካከል ከፊል አዲስ አበባ፣ ከፊል አማራ ( በተለይም ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደር እና ደቡብና ሰሜን ወሎ)፣ ድቡብ ክልል፣ ሶማሊ ክልል፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ፣ ከኦሮምያ ክልል ደግሞ ጅማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ወረዳዎች ናቸው።

ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ( ኢዜማ) እንደ ብልጽግና ፓርቲ ሁሉ አገራዊ ፓርቲ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሶሻል ዲሞክራሲ ( ማህበራዊ ፍትህ)ን መሰረት ያደረገ ስርዓት እንዲመሰረት ይታገላል። ታዋቂ የሆኑ ፖለቲከኞችንና ምሁራንን አካቷል። በተለያዩ አገሮች ከብልጽግና በመቀጠል ሰፊ የማደራጀት ስራ ሰርቷል። ፓርቲው በምርጫ ክርክር ወቅት አቅሙን በማሳየት ለማሸነፍ ተስፋ አድርጓል።

ኢዜማ ጥሩ የሚባል የፖለቲካ ፕሮገራም ቢኖረውም፣ ከብልጽግና ጋር አብሮ በደጋፊነት ይሰራል መባሉ፣ በአገሪቱ አንዳንድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ እስከ ቀርብ ጊዜ ድረስ ዝምታን መምረጡ እንዲሁም መንግስትን በማገዝ ስም ራሱን ከፖለቲካ እንዳገለለ ተደርጎ ሲተች መቆየቱ በሚፈለገው ደረጃ ህዝባዊ ድጋፍ እንዳያገኝ አደርጎታል። የአማራ ብሄርተኞች በተዳጋጋሚ ጸረ አማራ ድርጅት አድርገው ለማሳየት የሄዱበት ርቀት እና ድርጅቱም ከሚቀርብበት ክስ እራሱን ለመከላከል የሰራው ስራ አነስተኛ መሆኑ፣ በኢዜማ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው የቀድሞ የግንቦት7 መሪዎች ከአማራ ህዝብ ጋር በተያያዘ የሚቀርብባቸው ውንጀላ እንዲሁም የኦሮሞ ብሄርተኛ አክቲቪስቶች ድርጅቱን የአማራ ጉዳይ አስፈጻሚ አድርገው መፈረጃቸውና በተለያዩ ያገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ ቅስቅሳ ለማድረግ አለመቻሉ በፓርቲው የመመረጥ እድል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ክስተቶች ናቸው።

ኢዜማ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ክልል በተለይ በጉራጌና በአርባምንጭ ዞኖች መጠነኛ የአሸናፊነት ድምጾችን ሊያገኝ ይችላል። የፓርቲው ውጤት በምርጫው ክርክር ወቅት በሚያሳየው ብቃት የሚለካ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ድፍሮ ይህን ያክል ድምጽ ያገኛል ማለት አይቻልም። የኢዜማ አብዛኛው ደጋፊ ምሁራኑ ክፍል ሲሆን፣ በብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ በተሳበው ወጣት በኩል ያለው ተቀባይነት አነስተኛ ነው።

ኦፌኮ

በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ አቶ ጃዋርን በአባልነት ከተቀበለና የኦኤምኤንን ድጋፍ ካገኘ በሁዋላ፣ በኦሮምያ ክልል ያለው ተቀባይነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ይህ ነው የሚባል ራዕይና የፖለቲካ ፕሮግራም የሌለው ድርጅት ቢሆንም፣ አብዛኛቸው ፕሮግራሙ ፌደራሊዝሙን በማስቀጠል ላይ ያጠነጠነ ነው። ኦፌኮ የወጣቱን ስሜት ሊይዙ በሚችሉ የልዩነት ፖለቲካ ላይ አትኩሮ እየሰራ ነው። ኦፌኮ በታሪክ ተበድለናል የሚሉትን በአብዛኛው እስልምና ተከታይ የሆኑትን ኦሮሞዎች ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚችል ይተነበያል።

ይሁን እንጅ መሪዎቹ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎ ያላቸው ተቀባይነት እጅግ አነስተኛ ነው። በአጋጣሚ በኦሮምያ ክልል ቢያሸንፉ እንኳን ከሌሎች ክልል ባለስልጣናት ጋር ተጣምረው አገር ለመምራት የሚችሉበት እድል አናሳ ነው።

ምርጫ ቦርድ በአቶ ጀዋር መሃመድ ላይ የጀመረውን የዜግነት ጥያቄ የሚያነሳ ከሆነ፣ አቶ ጃዋር በምርጫው የመሳተፍ እድል ያገኛሉ። ኦፌኮ አሁን ባለው ቁመናው በምስራቅ ሃረርጌ፣ በአርሲና በባሌ እንዲሁም በአንቦና በመሳሰሉት በአብዛኛው ወጣቶች በሚበዙባቸው ከተሞች ሊያሸንፍ ይችላል። የኦሮምያ ክልልን የፓርላማ ወንበር ከብልጽግና ጋር ተካፍሎ የሚይዝበት እድል ሰፊ ነው።

ኦነግ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከስሙና እድሜው አንጻር ሲታይ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ነው። ኦነግ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማያደርግ፣ ወደፊት ወይም ወደ ሁዋላ እየተራመደ እንደሆነ በግልጽ የማይታወቅ ድርጅት ነው። በጃል መሮ ከሚመራው ኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ምክንያት በኦነግ አባላት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሲደርስ ቆይቷል ። ኦነግ እንደ ኦፌኮ ወጣቶችን በስሜት አነሳስተው ከጎኑ ሊያስልፉለት የሚችሉ ፖለቲከኞች የሉትም። አብዛኞቹ መሪዎችም በእድሜ የገፉ ናቸው። ኦነግ ምናልባትም የተወሰኑ ወንበሮችን በወለጋና በቦረና አካባቢዎች ሊያገኝ ይችላል ተብሎ ይገመታል።

አብን

በአቶ በለጠ ሞላ የሚመራው አብን የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም ክስተት ከፈጠረበት ድባብ ለመውጣት እየሞከረ ነው። በአስተሳሰብ ደረጃ ለአማራ ህዝብ እንደሚታገል ቢያስታውቅም ፣ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ከሌሎች ብሄር ተኮር ድርጅቶች ጋር የተለየ አቋም ያለው መሆኑ ለወደፊቱ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ወንበር ቢያገኝ እንኳን ጥምርት እንዴት እንደሚፈጥር ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ስትራቴጂ ይዞ ለመቅረብ ሲሳነው ይታያል። ከማን ጋር መጣመር እንዳለበትም መወሰን ያቃተው ድርጅት ነው። እንደ ኦፌኮ ሁሉ ወጣቶችን በስሜት አስነስተው የፖለቲካ ድጋፍ ሊያሰባስቡ የሚችሉ አመራሮች ከሰኔ 15 ክስተት ጋር በተያያዘ በስር ቤት መቆየታቸው የድርጅቱን ፈጣን እድገት ገቶታል። የድርጅቱ ስም ከጄ/ል አሳምነው ጋር አብሮ መነሳቱም በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በደቡብና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች የነበረውን ድጋፍ ሊሸረሽርበት ይችላል።

ምንም እንኳን በአማራ ወጣቶች ዘንድ አሁንም ተመራጭ ድርጅት ቢሆንም፣ ከሰኔ 15 ጋር በተያያዘ የሚነሳበትን ክስ በበቂ ሁኔታ በማስረዳት ገጽታውን ካልቀየረ፣ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚፈልገውን ድምጽ ላያገኝ ይችላል። በተለይም በሰሜንና ደቡብ ጎንደር እንዲሁን በደቡብ ወሎ ፓርቲው ድምጽ ለማግኘት እንደሚከብደው መረጃዎች ያሳያሉ።

በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን የፓርላማ ወንበር ይዞ ቢቅጥልም፣ አብንም ሁለተኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ እንደሚወጣ ይገመታል።

https://ethio-redfox.com/

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: