አልጀዚራ በአባይ ጉዳይ ላይ ለምን ትኩረት ሰጠ?

(ERF) ታዋቂው አልጀዚራ ሚዲያ ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ተከታትይነት ያላቸውን ዘገባዎች እያቀረበ ይገኛል። በቅርቡ በግድቡ ዙሪያ ከሰራው ዘጋቢ ፊልም በተጨማሪ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን ቃለ ምልልስ አድርጓል። ከሌሎች የአረብ ሚዲያዎች በተለዬ አልጀዚራ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ስሜት እያንጸባረቀ መሆኑ፣ ሚዲያው የአረብ አገራት ከያዙት አቋም የተለዬ ዘጋብ እንዴት ሊያቀርብ ቻለ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእርግጥም አልጀዚራ ከሌሎች ተመሳሳይ ሚዲያዎች ጋር ሲተያይ ፕሮፌሽናል ዘገባዎችን የሚያቀርብ ሚዲያ ነው፤ ይሁን እንጅ እንደ ሌሎች ሚዲያዎች ሁሉ አልፎ አልፎ ለአረብ ፖለቲካ በተለይም ለካታር የሚያደላ ዘገባ ሲሰራ እንደነበር ብዙዎች የሚመሰክሩት ነው። የአረብ አገራት በካታር ላይ የጉዞ እቀባ ሲጥሉ አልጀዚራ እርምጃውን የሚኮንን ዘገባዎችን ሲሰራ ታይቷል።

አልጀዚራ በካታር መንግስት የተመሰረተና አሁንም ድረስ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ሚዲያ ነው። ሚዲያው ሌሎች የአረብ አገራትን የሚተቸውን ያክል የካታርን መንግስት ለመተቸት አይደፍርም።  ብዙ የአረብ አገሮች አልጀዚራን የካታር መንግስት የውጭ ጉዳይ አስፈጻሚ አድርገው ይቆጥሩታል። ሳውድ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ እና ባህሬን ከካታር ጋር ያላቸውን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ሲያቋርጡና በአገሪቱም ላይ የጉዞ ማዕቀብ በመጣል ከበባ ሲፈጽሙ አንዱ ምክንያታቸው አልጀዚራ ነው። እነዚህ አገሮች ካታር ሽብርተኞችን መርዳት እንድታቆም፣ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ፣ ለቱርክ የሰጠችውን ወታደራዊ ቤዝ እንድትሰርዝና አልጀዚራን እንድተዘጋ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል። በእነዚህ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ዛሬም ድረስ እንደተበላሸ ነው።

በግብጽ እና በአልጀዚራ መካከል የተጀመረው አለመግባባት በቅድሞው የግብጽ መሪ ሁሴን ሙባረክ ዘመን የተጀመረ ሲሆን፣ ሙባረክ ዶሃ የሚገኘውን የአልጀዚራን ቢሮ ሲጎበኙ “ ይች ትንሽ ክብሪት ናት” እንዲህ አገር የምታቀጣጥለው ብለው መናገራቸው ተዘግቧል። ሙባረክ ከተወገዱ በሁዋላ ስልጣን ላይ የወጣው የሙሃመድ ሙርሲው እስላማዊ ወንድማማቾች ( Muslim Brotherhood) የካታር ድጋፍ የነበረው ሲሆን፣ አሁን ስልጣን ላይ የሚገኙት አል ሲሲ የሙርሲን መንግስት አስወግደው ስልጣኑን ሲይዙ ደግሞ አልጀዚራ ተከታታይ ዘገባዎችን እየሰራ ጸረ ዲሞክራሲ፣ ህገ ወጥና አምባገነን መሪ አድርጎ ለማሳየት ጥሯል። የግብጽ መሪዎችም 3 የአልጀዚራ ጋዜጠኞችን በማሰርና ጽ/ቤታቸውን በመዝጋት በአልጀዚራ ላይ የበቀል ዱላቸውን አሳርፈዋል።

አልጀዚራ በአል ሲሲ መንግስት ላይ የሚሰራው ዘገባ የግብጽ ባለስልጣናትን ዘወትር እንዳበሳጨ ነው። አልጀዚራ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የሚታየውን ፍጥጫ አስመልክቶ ኢትዮጵያን ማእከል አድርጎ ዘገባዎችን ቢሰራ ብዙም አይገርምም። አሁን ባለው ሁኔታ የሚፈጸም ባይሆን፣ ካታርና ግብጽ ግንኙነታቸውን ቢጀምሩ የአልጀዚራም ትኩረት ሊቀየር ይችላል።

ኢትዮጵያ ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስና ከሳውድ አረቢያ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት አላት ። ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስን ሲጎበኙ ብዙ የዲፕሎማሲ ውጤቶችን አግኝተዋል። ይሁን እንጅ እነዚህ አገሮች ከካታር፣ ቱርክና ኢራን ጋር በተያያዘ ከግብጽ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ጥብቅ ነው። ግብጽን እንደ መከታ የሚያዩ በመሆኑ፣ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላችሁን ግንኙነት አቋርጡ ብትላቸው ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ካታርም ይህን እድል ተጠቅማ ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ወዳጅነት ልትመሰርት ትችላለች ።

አልጀዚራ አሁን ባለበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ በጎ ሽፋን መስጠቱ መልካም ነው፤ ዘላቂ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ግን አይቻልም። ሁሉንም ነገር የሚወሰነው የካታርና የግብጽ ግንኙነት ነው።  

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: