የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ኮሮናን አስታከው ዋጋ ከመጨመር ይቆጠቡ!

( ERF) አንዳንድ ብሄራዊ አደጋዎች ሲከሰቱ ነጋዴዎች የዜግነት ግዴታ ተሰምቷቸው ምርቶቻቸውን ቢችሉ በቅናሽ ዋጋ ካለሆነም በገበያ ዋጋ መሸጥ ሲገባቸው፣ ከችግሩ ለማትረፍ የሚያደርጉት ሩጭ ብዙዎችን እያበሳጨ ነው ። በእርግጥም የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነገር ሲያጋጥም ከህዝቡ ጋር ሆነው ችግሩን መጋራትና ችግሩ እንዲቀረፍ መርዳት እንጅ በህዝቡ ጉዳት ለማትረፍ መሯሯጥ አይገባቸውም ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰዎች ናቸው፤ የሰው ልጅ ሲጎዳ ማዘን ነገ በራስ ላይ ጉዳት ሲደርስ አዘኔታ ለማግኘት እንደሚጠቅም ማወቅ ነበረባቸው። የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ድርቅ አጋጠመ ሲባል ወይም ጦርነት ሊነሳ ነው ሲባል ወይም ሆን ብለው መዓት በማስወራት ዋጋ ያንሩና ደሃውን ሲጎዱት ቆይተዋል። ድሃው የእለት ጉርሱን ለማግኘት አልሞላለት ብሎ ላይ ታች እያለ ባክኖ ቤቱ ገብቶ ያገኛትን ቀምሶ ካልሆነም ጾሙን አድሮ ሲተኛ፣ እነሱ በእሱ ጭንቀትና ላብ ባተረፉት ገንዘብ ጮማ እየቆረጡ በውስኪና በቢራ እያወራረዱ ከውሽሞቻቸው ጋር ሌሊቱን ያነጉበታል።

የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ በሚል በአንድ ቀን የእጅ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። ነገ ደግሞ የሸቀጥ ዋጋ በ10 እጥፍ ይጨምራል። በሌሎች አገሮች ድሆች እንዳይጎዱ ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን በፍጥነት በቅናሽ ዋና ሲያቀርቡ፣ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች፣ ምርቶቻቸውን እየደበቁ ዋና ያንራሉ። አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

ህዝቡ ነጋዴዎች ዋጋ እንዳይጨምሩ ፍርሃቱን አቁሞ ተረጋግቶ የእለት ፍጆታውን ብቻ ሊገዛ ይገባል። መንግስትም በሞት በሚያተርፉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር አድርጎ በህዝብ እንዲዋረዱ በማድረግ የማሸማቀቅ ( shaming) እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት አለበት ። ደሃው ያለ ችግር የእለት ፍጆታውን የሚያገኝበትን መንገድም ከአሁኑ ለማመቻቸት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ግድ ይለዋል።

ነጋዴዎች የዜግነት ሃላፊነት ተሰምቷችሁ ዋጋ ባለመጨመር አገራችሁን መታደግ ካልቻላችሁ፣ የዜግነት ግዴታችሁን እንዳልተወጣችሁ ይቆጠራል። እናንተ ነግዳችሁ የሚያልፍላችሁ ህዝብ ሲኖር ነውና ቅድሚያ ህዝባችሁ በጤና እንዲኖር ዋጋ ባለመጨመር ተባበሩ።አሁንም ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በእቃዎች ላይ የቆለላችሁትን ዋጋ አውርዱ!

ERF

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: