የኢትዮጵያ ወታደራዊ መኮንኖች የአባይ ግድብ ጉብኝት መልዕክቱ ምንድነው?

( ERF) የኢትዮጵያ አየር ሃይል ቁመና ምን ይመስላል?

በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለው ፍጥጫ እየተካረረ በመሄድ ላይ ነው። ግብጽ ከዲፕሎማሲ ዘመቻ በተጨማሪ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረች ነው። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት እየዞሩ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየወተወቱ ነው። ኢትዮጵያም በቀድሞው ፕ/ት በዶ/ር ሙላቱ ተሾመና በፕ/ት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ተለያዩ አገሮች በመላክ የግብጽን ዘመቻ ለማክሸፍ እየጣረች ነው። በሌል በኩል የግብጽ ወታደራዊ አዛዦች፣ ማንኛውም ወታደራዊ አማራጭ ዝግ አይደለም ይላሉ።ይህን ተከትሎ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ የመከላከያ አዛዦችን ሰብስበው ከአናገሩ በሁዋላ “ሰራዊቱ የአገሩን ድንበር ለመጠበቅ ዝግጁነቱን አረጋግጦልኛል፣ እኔም በሰራዊቱ ሞራል ኮርቻለሁ” ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ዋና አዛዦች ወደ አባይ ግድብ በመሄድ ስራውን ተመልክተዋል። የአየር ሃይል አዛዡ ብ/ጄ ይልማ መርዳሳ በግድቡ ላይ የሚወሰድን የአየር ላይ ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ም/ክ የመከላከያ ኢታማዦር ሹሙ ጄ/ል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የልዑካን ቡድን ደግሞ ወደ ሱዳን አቅንቷል። ዋና አላማው ግብጽ በሱዳን የአረብ ሊግ ውሳኔ የተነሳ የበቀል እርምጃ ብትወስድ ኢትዮጵያ እገዛ እንደምታደርግ ለመግለጽ እንዲሁም ሱዳን ለግብጽ የአየር እና የየብስ ክልሏን እንዳትሰጥ ማረጋገጫ ለማግኘት ነው። የአረብ ሊግ አገራት የሆኑት ሳውድ አረቢያና ዩናይት አረብ ኢሚሬትስ ለሱዳን የሚሰጡትን እርዳታ በማቆማቸው ሱዳን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሟታል። በዚህ የተነሳ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ሊነሳ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ኢትዮጵያ ሱዳንን በማረጋጋት አገሪቱ ከግብጽ ጎን እንዳትሰለፍ ለማድረግ ከፍተኛ ሃላፊነት ወድቆባታል። የኢትዮጵያ የጦር መኮንኖች በግልጽ እያስተላለፉት ያለው መልዕክት ግብጽ በአባይ ግድብ ላይ የሃይል እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን የሚያመለክት ነው።

ግብጽ በግድቡ ላይ የሃይል እርምጃ ብትወስድ ኢትዮጵያም የሱዳንን የአየር ክልል ተጠቅማ የአጸፋ እርምጃ ትወስዳለች ። ይህን ለማድረግ ግን የሱዳንን የአየር ክልል ፈቃድ ማግኘት አለባት ። አሁን ባለው የሁለቱ አገራት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሱዳን ለራሷ እድል ስትል ግብጽ የአየር ክልሏን ጥሳ በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ከወሰደች፣ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ እርምጃ ብትወስድ የተቃውሞ ድምጿን ከማሰማት ትቆጠባለች።

ኢትዮጵያ ይህን ለማድረግ ወታደራዊ ብቃቷን ማዘመን ወሳኝ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከግብጽ የሚሰነዘርን ጥቃት ለመመከት በቂ አቅም አለው። አየር ሃይሉ ልምድ ያላቸው አብራሪዎችና እና ዘመናዊ የሚባሉ የጦር ጀቶች አሉት ። ግብጽ በጦር ጀት ዘመናዊነትና ብዛት በተለይም ኤፍ 16ን የመሳሰሉ አደገኛ የጦር ጀቶች በመያዝ ከኢትዮጵያ ብትበልጥም ፣ ከቦታ እርቀት አንጻር የኢትዮጵያ የጦር ጀቶች ጥቃት ለማድረስም ሆነ ለመመከት የኢትዮጵያ ሱ 27 የጦር ጀቶች የተሻለ እድል አላቸው። ኢትዮጵያ ግድቡን ለመጠበቅ ከሩስያና ከቻይና የገዛቻቸው የአየር መቃወሚያዎችም የግብጽን አየር ሃይል ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ወታደራዊ አዛዦች በአላቸው ወታደራዊ አደረጃጀት ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: