ዶ/ር አብይ አህመድ በፌስቡክ የድጋፍ ድምጽ የቀዳሚነቱን ስፍራ እንደያዙ ቀጥለዋል

( ERF) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረጅም ጊዜ በኦፌኮው አባል አቶ ጀዋር መሃመድ ተይዞ የነበረውን የኢትዮጵያን የፌስቡክ የድጋፍ ( ላይክ) ቁጥር መሪነት የተረከቡ ሲሆን፣ በተከታይ ብዛት (followers) ቁጥር ግን አሁንም አቶ ጀዋር እየመራ ነው። ይሁን እንጅ ዶ/ር አብይ የፌስቡክ ገጻቸውን በቅርቡ የጀመሩ በመሆናቸው በተከታይ ብዛት አንሰው ቢገኙም፣ የተከታዩ ቁጥር አሁን በሚታየው ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት ጥቂት  ወሮች ውስጥ የመሪነቱ ስፍራ ይይዛሉ።  

አቶ ጀዋር ከ9 ዓመታት በፊት በከፈቱት ፌስቡክ ወድ 1 ሚሊዮን 800 ሺ ተከታዮች ሲኖራቸው፣ ዶ/ር አብይ በ3 ወራት ውስጥ ብቻ ከ 900 ሺ ያላነሱ ተከታዮችን አፍርተዋል። ተከታይን በፍጥነት በማሰባሰብ ከታዬ ዶ/ር አብይ ከኢትዮጵያ ፌስቡከሮች ሁሉ ቀዳሚ ይሆናሉ።

ሁለቱ ፖለቲከኖች የሚለጥፉዋቸውን ጽሁፎች በሚደግፉ ሰዎች “ ላይኮች” ብዛት ሲታይ ደግሞ፣ ዶ/ር አብይ አቶ ጀዋርን በአማካኝ በ5 እጥፍ ይበልጧቸዋል። የዶ/ር አብይ ድጋፍ ( ላይክ) በአማካኝ ከ15 ሺ ሲሆን፣ የአቶ ጀዋር አማካኝ የድጋፍ መጠን  ደግሞ  3 ሺ ነው። የአማካኝ መጠኑ ስሌት ከፍተኛውና ዝቅተኛው ተወስዶ የተሰላ ነው።

አቶ ጀዋር አብዛኛውን ተከታይ ያፈሩት (followers) በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ ይካሄድ በነበረበት በ 2008 እና 2009 ዓም ነበር። ዶ/ር አብይ የአቶ ጀዋርን የፌስቡክ ድጋፍ በመቀነስ የወጣቱን ድጋፍ ለማግኘት የቀየሱት ዘዴ እንደተሳካላቸው ይነገራል። አብይ አህመድ አሊ የሚለው ፌስቡክ እንደተከፈተ የዶ/ር አብይ ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ሲጨምር፣ የአቶ ጀዋር ግን ከሞላ ጎደል በአለበት እንደቆመ የሁሉም ፌስቡኮች መረጃዎች ያሳያሉ። ዶ/ር አብይ በፌስቡክ ማወዳደሪያ መስፈርት ከ 5 ፣ 4.7 አግኝተዋል።

በድጋፍ አስተያየት ሰጭዎች ደረጃ ሲታይ ደግሞ የአቶ ጀዋር ደጋፊዎች አብዛኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሲሆኑ፣ የዶ/ር አብይ ዳጋፊዎች ግን የተለያዩ ብሄሮችን ያካተቱ ናቸው። ሁለቱም ጽሁፎችን በ3 ቋንቋዎች ማለትም በእንግሊዝኛ፣ አማርኛና ኦሮምኛ መጻፋቸው ያመሳስላቸዋል። የዶ/ር አብይ የፌስቡክ መልዕክት በአብዛኛው በእለት ውሏቸውና አገራዊ አንድነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ የአቶ ጀዋር ደግሞ በኦሮሞ ፖለቲካና የመንግስትን ፖሊሲ በመተቸት ላይ ያነጣጠረ ነው።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: