“ የሚጠሉ ከኮረና ቫይረስ ባልተናነሰ ውስጣቸውን ይበላሉ” ዶ/ር አብይ አህመድ
ፓርቲው ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል። የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብይ አህመድ ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እንዳሉ ገልጸዋል። በእነዚህ ዝግጅቶች የሚገኘውን ገቢ ለህዝብ ማስታወቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እናካፍላለን ብለዋል።
ዶ/ር አብይ “ የሚጠሉ ሰዎች፣ የሚጠየፉ ሰዎች፣ የማይወዱ ሰዎች ከኮረና ቫይረስ ባልተናነሰ ውስጣቸውን ይበላሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የመንግስት ገንዘብ ላለመጠቀም መውሰኑንም ተናግረዋል።
የኢዜማው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በቅርቡ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ህወሃት ሁሉ ባለሃብቶችን እያስገደደ ገንዘብ እየሰበሰ ነው በሚል በፓርቲው ላይ ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በዝግጅቱ ላይ ከተገኙት ባለሃብቶች ምን ያክሉ ገንዘብ በፍላጎታቸው እንደሰጡ አይታወቅም። ዶ/ር አብይም በንግግራቸው በኢዜማ ለቀረበው ክስ መልስ አልሰጡም።
“የፖለቲካ ሳይንቲስት ነን የሚሉት ኢትዮጵያውያን አንድም ቀበሌ መርተው አያውቁም” በማለት የኢትዮጵያን ምሁራንንና የፖለቲካ ሳይንቲስት ነን የሚሉትን አክቲቪስቶች ተችተዋል።
ዶ/ር አብይ ብልጽግና ካገኘው ገቢ ውስጥ 100 ሚሊዮን ብሩን ለድሆች ሳሙና መግዣ ይውል ዘንድ መለገሱንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን እንዲጸልዩ፣ የሳይንስን መመሪያ በመከተል እንዲታጠቡና ከመጨባበጥ እንዲታቀቡም ጠ/ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። ከዚህ ውጭ መፍራት እንደማይስፈልግ እና ህዝቡ እንዲረጋጋ ጠይቀዋል።
ዶ/ር አብይ ከተለያዩ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድ ወይም ለመደጋገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።