እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከ25 ሺ ብር በላይ እዳ አለበት

( ERF) የገንዘብ ሚኒስቴር የቅርብ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከውጭና ከአገር ውስጥ ባንኮች የተበደረችው የገንዘብ መጠን 79 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ከዚህ ውስጥ 53 ቢሊዮን 705 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ አገራት የተገኘ ብድር ሲሆን፣ 27 ቢልዮን 29 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከአገር ውስጥ ባንኮች የተገኘ ነው። ከውጭ እና ከአገር ውስጥ የተገኘው ብድር ለአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ሲካፈል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ 790 ዶላር ወይም ወደ 25 ሺ ብር እዳ አለበት ።

43 በመቶ የሚሆነው የውጭ እዳ ለተለያዩ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በረጅም ጊዜ የሚከፈል  ሲሆን፣ 31 በመቶ የሚሆነው ደግሞ   በአጭር ጊዜ የሚከፍል እዳ ነው። 73 በመቶ የሚሆነው የውጭ እዳ የሚከፈለው በአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ 15 በመቶው በዩሮ እና 5 በመቶው በቻይናው ዩአን ቀሪው 7 በመቶ በተለያዩ ገንዘቦች ይከፈላል።

ኢትዮጵያ አምና ለውጭ አበዳሪ ድርጅቶች 3 ቢሊዮን 264 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የፈጸመች ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ አበዳሪ ተቋማት ደግሞ 1 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ፈጽማለች ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ እዳ ከተጫናቸው አገራት ተርታ መመደቧን የገለጸው የገንዘብ ሚኒሰቴር፣ ይህ በአጭር ጊዜ የሚከፈለው እዳ ሲገባድደና ወደ ውጭ የሚላከው ምርት ሲጨምር ይስተካከላል የሚል እምነት አለው።

 አብዛኛው ብድር የተፈጸመው ህወሃት/ኢህአዴግ አገሪቱን ሲመራ በነበረበት ጊዜ ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በሙስና፣ ባልተጠኑ፣ ባለተጠናቀቁ ወይም በተበላሹ ፕሮጀክቶች ባክኖ ቀርቷል። ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ መክፈያቸው የደረሱ ብድሮች፣ የመክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘም የቻይና፣ የዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ፣ የሳውድ አረቢያን የጀርመን መንግስታትን ጠይቀው አወንታዊ መልስ በማግኘታቸው ኢትዮጵያ ብድራቸውን መክፈል ከማይችሉ አገራት ተርታ ከመመደብ ታድገዋታል። በቅርቡ አይ ኤምፍና የአለም ባንክ ከፍተኛ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ማበደራቸው ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ጥቅሟል። ይሁን እንጅ የኮሮና ቫይረስ በመጠኑም ቢሆን የተረጋጋውን ኢኮኖሚ፣ የበለጠ እንዳያበላሸው ትልቅ ስጋት አለ።  

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: