ከቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት የጦር መሳሪያዎች ለጀሃድ ወይስ ለንግድ?

( ERF) ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ከቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ባለፈው ሳምንት ብቻ 500 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ከ 13 ሺ በላይ ሽጉጦችና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በጅቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በሁዋላ ተይዘዋል። 25 የኢትዮጵያ፣ የመንና ቱርክ ዜጎችም እጃቸው አለበት በሚል በቁጥጥር ስር ውለዋል። የጦር መሳሪያዎቹ ዋነኛ መነሻ አገር ቱርክ መሆኗ ለምን የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በዚህ የጦር መሳሪያ ዝውውር የቱርክ መንግስት እጅ አለበት ?

በታይፕ ኤርዶጋን የሚመራው የቱርክ መንግስት የጦር መሳሪያ ዝውውሩ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የሚካሄድ ነው በማለት እጁ እንደሌለበት ይከራከራል። ለምን ቁጥጥር እንደማያደርግ ግን በበቂ ሁኔታ አያስረዳም። የኤርዶጋን መንግስት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን እንደሚያዘዋውር መረጃዎች ያሳያሉ።

ከ ሶስት ሳምንት በፊት የቱርክ ወታደራዊ አዛዦችን የያዘች መርከብ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጭና በድብቅ ወደ ሊቢያ ስታጓጉዝ በፈረንሳይና በጣሊያን የባህር ላይ ተቆጣጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውላለች ። የመርከቧ አዛዦችም በሮም ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የጦር መሳሪያው በሊቢያ የሚታየውን ግጭት ለማባባስ ተብሎ የተላከ መሆኑ ተዘግቧል። የቱርክ መንግስት በቅርቡ በሊቢያ ያለውን መንግስት ለመርዳት በሚል አለማቀፍ ተቃውሞ እየቀረበበት ተዋጊ ጀሃዲስቶችን ከመላክ አልተቆጠበም። አለማቀፉ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን ህግ በመጣስ ደግሞ መሳሪያ ሲያጓጉዝ ተይዟል።

እንዲሁም አምና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ ከቱርክ ወደ ናይጀሪያ ሲገባ በመያዙ የአገሪቱ ባለስልጣናት ዲፕሎማቶቻቸውን በፍጥነት ወደ ቱርክ በመላክ ቁጣቸውን ገልጸዋል። የናይጀሪያ ጋዜጦች  ኤርዶጋን በአለም ላይ የሚካሄዱ የጅሃድ ግጭቶችን በማባባስ በኩል ዋና ተጠያቂ ናቸው ሲሉም የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።    

የቱርክ መንግስት በግልጽ እስልምናን በሃይል ለማስፋፋት ያለመ የውጭ ፖሊሲ ይከተላል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ይቀርቡበታል። ከዚህ አንጻር ሲታይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት በመጠቀም፣ የኤርዶጋን የደህንነት ሰዎች ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አለመረጋጋት ለመፍጠር መሞከራቸው ግልጽ ይሆናል።

ቱርክ ከሳውድ አረቢያና ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ ጋር የገባችበትን ውዝግብ እና ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ጋር ያላት አወንታዊ ግንኙነት ግምት ውስጥ ሲገባ የቱርክ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ የጅሃድ ጦርነት ለማስነሳት አያስብም ማለት አይቻልም። ግብጽ የባህር ሃይል በሱዳንና በሶማሊያ ለማቋቋም ማሰቧም ጥርጣሬውን የጎላ ያደርገዋል።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተያዙት ሰዎች በሂደት እውነታውን የሚያወጡት ቢሆንም፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸው እና የተያዙበት አካባቢ ግምት ውስጥ ሲገባ ድርጊቱ፣ በቱርክ መንግስት የደህንነት አባላት ሆን ተብሎ የተቀናበረ እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በአለም ላይ የሚታወቁት በሰላማዊነታቸው እና ለአገራቸው ባላቸው ፍቅር ነው። ይሁን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ፣ አንዳንድ ግለሰቦች የውጭ አገራት ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመሆን በአገራቸው ላይ ክዳት እየፈጸሙ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: