ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የደቀነው አደጋና የገንዘብ ተቋማቱ ምላሽ

(ERF) አይ ኤም ኤፍና የአለም ባንክ በኮርና ቫይረስ የተነሳ በአለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚፈጠር አስጠንቅቀዋል። በተለይ በድሃ አገሮች ቀውሱ የከፋ ይሆናል ይላሉ። ኢትዮጵያም ተጎጂ ከሚሆኑ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህንን ችግር ለመቋቋም እንዲያስችል አይ ኤም ኤፍ 50 ቢሊዮን ዶላር ፣ የአለም ባንክ ደግሞ 12 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸውን አስታውቀዋል።

የገንዘብ ተቋማቱ ለድሃ አገሮች የእዳ ስረዛና እዳ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው በማድረግ፣ ገንዘቡን ለመድሃኒት ግዥና በሽተኞችን ለመንከባከብ እንዲያውሉት እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በያመቱ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝባቸው ዋና ዋና ተቋማቷ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ እየተጎዱ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ተቋማት አንዱ ቢሆንም፣ የተጓዦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢውንም አብሮ ይቀንሰዋል የሚል ስጋት አለ።

ቱሪዝም ሌላው የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት መስክ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር ቅናሽ እያሳየ ነው። ኢትዮጵያ ከምታዘጋጃቸው የተለያዩ አለማቀፍ ስብሰባዎች የውጭ ምንዛሬ የምታገኝ ቢሆንም፣ በበሽታው ምክንያት ብዙ አለማቀፍ ስብሰባዎች እየተሰረዙ ነው። እስካሁን ብዙም ቅናሽ ያላሳየው ከዲያስፖራው የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ነው። በአጠቃላይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው። በአለም ላይ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ በመዳከሙ የነተሳ ቡናን የመሳሰሉ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ምርቶችን በመላክ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል ተብሎ ተሰግቷል። በአጠቃላይ ሲታይ ኮሮና በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

አይ ኤም ኤፍ እና የአለም ባንክ እንደ ኢትዮጵያ ያሉትን አገራት ለመታደግ የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦች በድረ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: