ዶ/ር አብይ በአንድ ጀዋር የተነሳ ምሁራንን አያስከፉ

(ERF) ጠ/ሚ አብይ አህመድ ራሱን የፖለቲካ ሳይንስቲስት ነኝ ብሎ የሚጠራውን አቶ ጀዋር መሃመድን ለመወረፍ የተናገሩት ንግግር በመላው ምሁራን ላይ እንደተሰነዘረ ዱላ ተደርጎ በመወሰዱ ፌስቡክ ላይ የትችት ውርጅብኝ እያስተናገዱ ነው። አቶ ጃዋር ራሱን የሰቀለበት ቦታ ስሜታቸውን እንደያዘው ከንግግራቸው መረዳት አይከብድም። አቶ ጃዋር ስለራሱ ለመናገር ይሉኝታ የማይዘው፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ትንሽ ብሎ ያልገባው ሰው ነው። በአለማችን ታላላቅ አስተሳሰቦችን እንኳን ያመነጩ ምሁራን እራሳቸውን እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ እንጅ እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት አይቆጥሩም። ትንሽ እውቀት አደገኛ ነው እንደሚባለው አቶ ጃዋር ራሱን እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስትና እንደ ተዋጣለት ስትራቴጂስት አድርጎ ሲናገር በተደጋጋሚ ተሰምቷል። በደንብ የተማረ ሰው ራሱን እንደ አላዋቂ ይቆጥራል እንጅ አዋቂ ነኝ እያለ በየሚዲያው አይደነፋም። ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ “እኔ ማውቀው አለማወቄን ነው” ያለውም ለዚህ ነው። እውቀትን የሚደርስበት ሰው የለም፤ የሰው ልጅ የሚያያውቀው ከማያውቀው ጋር ሲነጻጸ እጅግ ኢምንት ነው። የሰው ልጅ ማወቅ ከሚኖርበት ውስጥ የስናፍጭ ቅንጣት ታክል እንኳን ገና አላወቀም። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ራስን አዋቂ አድርጎ ማቅረብ አላዋቂነት ካልሆነ ሌላ ምን ይባላል።

ጃዋር እራሱን ሳይንቲስት አድርጎ ቢያቀርብ የሚያዋርደው እራሱን እንጅ ማንንም አይደለም። እንደ ኢዲያሚን ዳዳ “ማርሻል ዶ/ር ሳይንቲስት ኢንጂነር ጀዋር መሃመድ” እያለ ራሱን ቢጠራ ማንንም ሊያስጨንቅ አይገባም። ይህን እየሰሙ የሚያወድሱትና የሚከተሉት የእሱ ብጤ አላዋቂዎች ይኖራሉ። ይከተሉት። ተከታዮቹ እውነቱን አውቀው እንዲከተሉት ማድረግ የሚቻለው ስራን ሰርቶ በማሳየት እንጅ እሱን በመተቸት አይደለም። እንዲህ አይነት ሰዎች በተተቹ ቁጥር ደጋፊ ይበዛላቸዋል።

ዶ/ር አብይ ጀዋር በየጊዜው እራሱን ከፍ እርሳቸውን ደግሞ ዝቅ አድርጎ የሚያይበት መንገድ ስሜታቸውን እንደጎዳው ግልጽ ነው። ዶ/ር አብይ ከማንም በላይ ከውትድርና ተነስተው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን መስራታቸው ያስከብራቸዋል። ለሌላው አርአያ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል እንጅ አያሳፍራቸውም። ታዲያ ለጀዋር መልስ እሰጣለሁ በሚል የሚናገሩት ንግግር የብዙ ምሁራንን ስሜት የሚጎዳና በጥርጣሬ እንዲታዩ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረባቸው። ለአንድ ጀዋር መልስ እሰጣለሁ በሚል በእውነት ለፍተው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙትን ሰዎች ሳይቀር የሚነካ አደገኛ ንግግር በመሆኑ መስተካከል አለበት። ዶ/ር አብይ ትምህርትን ቢጠሉ ኖሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ለመማር ፍላጎት ባላሳዩ ነበር። ጸረ ምሁር ተደርገው መወገዛቸው ስህተት ነው። እሳቸውም በጅምላ ምሁራንን ማውገዛቸው ስህተት ነው። ሁለቱም አደገኛ አስተያይቶች መቆም አለባቸው።

በዚህ አጋጣሚ የአገራችንን የትምህርትና የምርምር ስርዓት መፈተሽ እና ምሁራንን ህዝባቸውን እንዲረዱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: