ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መንግስት የወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም

( ERF) ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረሰን ለመከላከል ትምህርት ቤቶችን መዝጋቷ፣ ስፖርታዊ ጨዋታዎችንና ታላላቅ ስብሰባዎችን ማገዷ ተገቢ ነው። ውሳኔው ለ 2 ሳምንት ብቻ የሚቆይ ቢሆንም፣ እንደ በሽታው ስርጭት እየታየ ሊቀጥል ይችላል። ይህ ጥሩ እርምጃ ቢሆንም፣ በቂ ግን አይደለም። ብዙ ህዝብ የሚገናኝባቸውን ቦታዎች ለማገድ ጠንከር ያለ ውሳኔ አልተወሰነም። አንደኛው የሃይማኖትና የጸበል ቦታዎች ናቸው። መንግስት ህዝቡ ወደ አብያተ ክርስቲያናትና ወደ መስኪዶች ከመሄድ ቤቱ ሆኖ ጸሎት እንዲያደርስ፣ በየቀኑ ህዝብን ሰብስበው ስብከት የሚሰብኩ የሃማኖት አባቶችም ለሁለት ሳምንት ያክል እንዲታቀቡ መከልከል ነበረበት ። ሌሎች ሃይማኖታዊ በአላትም እንዲቀሩ ማሳሰብ ይጠበቅበት ነበር።

በሌላ በኩል ህዝቡ በአደባባይ የሚያደርጋቸውን የገበያ ቀናት ለ2 ሳምንት ያክል እንዲያቆም ሊደረግ ይገባ ነበር። በተለይ አርሶ አደሩን ከበሽታ ለመከላከል፣ ይህን ተከትሎ ከሚመጣ ችግር ለመታደግ፣ አርሶ አደሩን ወደ አደባባይ ገበያ እንዳይሄድ በመከልከል ከአደጋ መከላከል ትዕዛዝ መስጠት ይገባ ነበር። አርሶ አደሩ ታሞ ቤቱ ከተቀመጠ፣ በገበያ ላይ የሚያመጣው አደጋ እጅግ ከፍተኛ ነው። አብዛኛው አርሶ አደር ምርቱን ስብስቦ እንኳን ቢሆን፣ የሰበሰበውን ምርት ወደ ገበያ ካላቀረበ ችግር መከሰቱ አይቀርም። አርሶ አደሩ የፍጆታ እቃዎችን በቀላሉ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠር ተገቢ ነው። ቢያንስ ጨውና ዘይት ለማግኘት ሲል እንዳይደክም፣ በአቅራቢያው የሚያገኝበት መንገድ ቢመቻችለት መልካም ይሆናል። አርሶ አደሩ ምርቱን የሚሸጥበት ስርዓት መዘርጋትም ከመንግስት ይጠበቃል።

ሌላው ህዝብ የሚጨናነቅባቸው ቦታዎች የመንግስት መስርያ ቤቶች ናቸው። የግብር መክፈያ፣ የመብራት እና ውሃ፣ የትራንስፖርትና መገናኛ፣ የቴሌና የመሳሰሉት መስርያ ቤቶች አገልግሎታቸውን ማቋረጥ ቢከብዳቸውም እንኳ ህዝቡ አገልግሎት ለማግኘት ሲመጣ ተጨናንቆ እንዳይቆም ዘዴ መፍጠር አለባቸው። የመንግስት ሰራተኞች ተጨማሪ ሰአቶችን በመስራት የተፋጠነ አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል። መንግስት እንዲህ አይነት ጥብቅ ትዕዛዝ ማስተላለፍ አለበት ።

መከላከያ ሰራዊቱን ጨምሮ ለአገር ደህንነት ወሳኝ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስተማር እንዲሁም እንደ አባይ ገድብ ያሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን የሚሰሩ ሰራተኞችን ከበሽታው ለመጠበቅ ጉብኝቶችን ለጊዜው መከልከል የገባል።

ከሁሉም በላይ ጠ/ሚኒስትሩ ራሳቸው ጉብኝታቸውን፣ ጉዟቸውንና ከሰዎች ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ሊቀንሱ ይገባል። በዚህ ሰዓት እርሳቸው ታመው አለጋ ቢይዙ በአገሪቱ ላይ ሊመጣ የሚችለው አደጋ ቀላል አይደለም። ስለዚህ እርሳቸው አርአያ ሆነው ሌላውም ህዝብ ግንኙነቱን በስርዓት እንዲያደርግ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

ይህን የምንለው ህዝብን ለማስፈራራት ሳይሆን፣ ከሚመጣ ጉዳት አገርን ለመከላከል ነው። ህዝቡ ይህን በሽታ መከላከል የሚቻለው በሳይንሳዊ ዘዴ በመሆኑ ሳይንሳዊ ምክሮችን ሊከተል ይገባል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: