ኮሮና ቫይረስ ፖለቲካን በመተካት ቀዳሚ የመንግስትና የሚዲያ አጀንዳ ሆነ

( ERF) የአለም መንግስታት ዋና የትኩርት አቅጣጫ ኮሮና ቫይረስን በመከላከል ላይ ሆኗል። የቻይና፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኤሲያና አፍሪካ አገራት መሪዎች ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ጊዜያቸውን ኮሮና ቫይረስን በመከላከልና ቫይረሱ የሚያደርሰውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ለመቀነስ በመምከር ያጠፋሉ። በአለም ላይ ያሉ ዋና ዋና የሚባሉት የመገናኛ ብዙሃን ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚዲያ ሽፋናቸው ኮሮና ቫይረስ ላይ ሆኗል። ለወትሮው ዋና የሚዲያ አጀንዳ የነበረው ፖለቲካ ከ2 በመቶ የሚበልጥ የዜና ሽፋን አላገኘም። የኢኮኖሚ ዜና ከኮሮና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል።

ቢቢሲ ከ98 በመቶ በላይ፣ ሲ ኤ ኤን  ከ97 በመቶ በላይ፣ አልጀዚራ 99 በምቶ ፣ ፎክስ ኒውስ ከ95 በመቶ በላይ ፣ ረዩተርስ ከ 95 በመቶ በላይ የዜና ሽፋናቸው በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ላይ ያተኮረ ነው። ሲኤን ኤንና ፎክስ ኒውስ የኮሮና ቫይረስን የትራምፕን መንግስት ብቃት መለኪያ አድርገው በመውሰድ የድጋፍና የተቃውሞ ዘገባዎችን እየሰሩ ነው። ከዚህ ውጭ የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ከአፍሪካ ደግሞ የግብጽ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ ሚዲያዎች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የዜና ሽፋናቸው በኮሮና ላይ ያተኮረ ሆኗል። እስራኤል  የጠ/ሚ ቤንጃሚን ናታንያሁን መንግስት ፍጻሜ የሚያበስረውን በአዲስ መንግስት ምስረታ ላይ ትኩርት የሚያደርግ ዘገባዎችን ብታወጣም፣ ኮሮና ቫይረስ የሚዲያዎቿን 85 በመቶ ሽፋን ይዟል።

በኢትዮጵያ የመንግስት ሚዲያዎች ዘግይተውም ቢሆን ዋና የዜና ሽፋናቸውን ኮሮና ላይ አድርገዋል። ኢቲቪ፣ ፋና እና የክልል ሚዲያዎች ከ 70 በመቶ ያላነሰ የዜና ሽፋን ሲሰጡ፣ የግል ሚዲያዎችም ከዚህ ቁጥር ያላነሰ ሽፋን ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚታይበት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ በተለይ ፌስቡክ፣ ከፖለቲካ ወደ ኮሮና ቫይረስ ፊቱን አዙሯል። ዋና ዋና የሚባሉት የፌስቡከ ጸሃፊዎች  አብዛኛው ትኩረታቸው  ኮሮና ቫይረስ ላይ ሆኗል። ብዙዎቹ ጸሃፊዎች ባህላዊ መድሃኒቶችን በማስተዋወቅ፣ መንግስት ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወሰድ ግፊት በማድረግና አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተሉ በማሰራጨት ላይ ተጠምደዋል።

 የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በዚህ ፍጥነት ከጨመረና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ፣ ሚዲያዎች ከፖለቲካ አጀንዳ ወጥተው በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ክብረ ወሰን ይሰብራሉ።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: