የምግብ ጦርነት እንዳይነሳ መንግስት ምን ያክል እየተዘጋጀ ነው?

( ERF) ኮሮና ቫይረስ በቀጥታ በሰዎች ህይወት ላይ ከደቀነው አደጋ በላይ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚፈጥረው አደጋ የከፋ እንደሚሆን ምልክቶች እየታዩ ነው። ህዝቡ ከአሁኑ ለመጠባበቂያ የሚሆን አስቤዛ ለመግዛት ሲጣደፍ እያየን ነው። ይህን ተከትሎም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል። የፌደራሉ መንግስት ከ 180 በላይ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎችን መቅጣቱን አሳውቋል። የአማራ ክልል ደግሞ የዚህን ሶስት እጥፍ የሚያክል ነጋዴዎችን መቅጣቱን ተናግሯል። አደጋው ግን በቅጣት ብቻ የሚቆም አይደለም። ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠይቃል።

በመጀመሪያ አርሶአደሩ ፈርቶ ቤት ከተቀመጠ እህል ወደ ገበያ ስለማይቀርብ የዋጋ ንረት ይከሰታል።ያለችውን መጠነኛ እህል የሚገዙትም ሃብታሞች ብቻ ይሆናሉ። አብዛኛው ደሃ ህዝብ በረሃብ የማለቅ አደጋ ተጋርጦበታል። ድሆችና ሃብታሞች የህልውና ትግል የሚያደርጉበት ሁኔታ ሊመጣ ስለሚችል መንግስት ይህን አስቀድሞ ለመከላከል በምግብ አቅርቦት ላይ ትኩርት ሰጥቶ መስራት አለበት። የምግብ እህል እጥረት ዋነኛ የእርስ በርስ ግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም። የመጠባበቂ እህል ካለ ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ፣ እህል እንዳይባክን መቆጣጠርና ትርፍ ለማግበስበስ በሚል እህል የሚከዝኑ ነጋዴዎችን እያስገደዱ ወይም በገበያ ዋጋ እየገዙ እህላቸውን እንዲሸጡ ማድረግ ይገባል።

ሌላው አብዛኛው ህዝብ በሽታውን ፈርቶ ቤቱ የሚቀመጥ ከሆነ ገቢው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ አይቀርም። ብዙ የንግድ ድርጅቶችና ኩባንያዎችም ሊዘጉ ይችላሉ። ገቢ ከቀነሰ ደግሞ ህዝቡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ለመግዛት አይችልም። ይህንንም ለመቋቋም መንግስት ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት። ኩባንያዎች እንዳይዘጉ፣ ከተዘጉም ሰራተኞች ምግብ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባዋል።

ዩኒቨርስቲዎች እና እስር ቤቶች ዋና ተጋላጭ ቦታዎች ናቸው። በእነዚህ ቦታዎች ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።በጥቃቅን ወንጀሎች የታሰሩ ካሉ እነሱን በመልቀቅ ወይም በዋስትና በመፍታት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ይገባል። የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ከግቢ እንዳይወጡ በመከልከል ወይም ቶሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ በማድረግ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድም እንዲሁ ተገቢ ነው እንላለን።

አብያተክርስቲያናትና መስጊዶችም እንደ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ሊዘጉ ይገባዋል!

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እጃቸውን በአስታጣቢ ሲታጠቡ ከማሳየት በላይ ጠንካራ እርምጃዎችን በመውሰድ ዜጎችን ከሚመጣ ችግር ለመታደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አሁን በሚታየው ሁኔታ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ፣ ስብሰባ ወዳዶቹ የመንግስት ባለስልጣናት ሁሉ መያዛቸው አይቀርም። ይህ ከሆነ ደግሞ ህዝብን የሚያስተባበር ሰው ሊጠፋ ይችላል። በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ታከለ ኡማ የሚያደርጉት ሁለገብ እንቅስቃሴ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። ጠ/ሚኒስትር አብይም ቢዘገዩም፣ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን መጀመራቸው መልካም ነው። ከእርሳቸው ግን ብዙ ይጠበቃል።

ወጣቶችን አደራጅቶ በበሽታው የሚጠቁ አቅመ ደካሞችን እንዲረዱ ከወዲሁ ማዘጋጀት ይገባል።

የኮሮና ፋይረስ በሽታን ተከትሎ ከሚመጣ ስርዓት አልበኝነት አገርን ለመካለከል የጸጥታ አካላት ልዩ ሃላፊነት አለባቸው።

እስካሁን የተወሰዱት እርምጃዎች መልካም ቢሆኑም በቂ አይደሉም። የአለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና ማሳደር አለበት።

www.ethio-redfox.com

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: