የኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም ግብጽን መፈናፈኛ እያሳጣት ነው

( ERF) ግብጽ ለዘመናት በበላይነት ይዛው የነበረው የአባይ ውሃ ድርሻ እንዳይነካባት ለማድረግ ከዲፕሎማሲ ዘመቻዎች በተጨማሪ ወታደራዊ ማስፈራሪያዎችን ስታደርግ ቆይታለች ። ትልቅ ተስፋ የጣለችባቸው ፕ/ት ትራምፕ እንዳሰቡት የኢትዮጵያን እጅ ጠምዝዘው የግብጽን ፍላጎት ማስፈጸም አልቻሉም። ከምዕራባውያን ብዙ እርዳታ የምታገኘው ኢትዮጵያ በቀላሉ ለአሜሪካ ጫና እጅ ትሰጣላች ተብሎ ቢጠበቅም፣ የአብይ ካቢኔ ሉአላዊነታችንን በገንዘብ አንለውጥም በሚል በወሰደው ጠንካራ እርምጃ ፣ አሜሪካ በመጨረሻ ጅራቷን ቆልፏ ለማፈግፈግ ተገዳለች ። ይህም ለኢትዮጵያ አንድ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ተወስዷል። ፕ/ት ትራምፕ በሚቀጥሉት ወራት በኮሮና ቫይረስ ስርጭትና በሽታው ይዞት በሚመጣው የኢኮኖሚ አደጋ ላይ የሚጠመዱ በመሆኑ፣ ለግብጽ የሚሆን ጊዜ አይኖራቸውም። ከዚያ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ምርጫ በመሆኑ፣ ፕሬዚዳንቱም ሆኑ ጉዳዩን በበላይነት የያዙት የግምጃ ቤት ሃላፊያቸው የግብጽ ጉዳይ ብዙም የሚያስጨንቃቸው አይሆንም። በፕ/ት ትራምፕ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላሉ የሚባሉት የግብጹ መሪ ፕ/ት ኤል ሲሲ ወዳጅ የሆኑት የእስራኤሉ መሪ ቤንጃሚን ናትንያሁም ከረጅም ጊዜ በሁዋላ ስልጣን የሚያስረክቡ በመሆኑ፣ ፕ/ት ትራምፕ ለጉዳዩ የሚሰጡትን ትኩረት ለመቀነስ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል።

ግብጽ የአረብ መንግስታትን አሳምና በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሄደችበት እርቀት በአለቀ ሰዓት በሱዳን በመጨናገፉ እንዳሰበችው እየሄደላት አይደለም። እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ወይም ሌሎች እርምጃዎችን እወስዳለሁ ብሎ የዛተ የአረብ አገር የለም። ጅቡቲና ሶማሊያ እንኳን ትዝብትን ከማትረፍ ውጭ ደፍረው እርምጃ አልወሰዱም። ኢትዮጵያ ጅቡቲና ሶማሊያ ለያዙት አሳፋሪ አቋም በሄደት ትቀጣቸዋለች ተብሎ ይጠበቃል።

ግብጽ በግድቡ ላይ የሃይል እርምጃ ለመውሰደ የነበራት እቅድም እንደአሰበችው የሚሳካ አይደለም። የኢትዮጵያ መከላከያ ግድቡን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ምላሽ መስጠቱ እንዲሁም ሱዳን ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት ጥሩ አለመሆኑ፣ ወታደራዊው አማራጭም በቀላሉ የሚተገበር አይደለም። ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅሟ ከግብጽ ጋር መወዳደር አትችልም። የአለምን አገሮች ባላቸው ወታደራዊ ጥንካሬ የሚያወዳድረው ግሎባል ፋየር ፓወር የተባለው ድርጅት ግብጽን ከአለም በ9ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት ፣ ኢትዮጵያን በ60ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። በተዋጊ ጀቶች ብዛት ሲታይ፣ ግብጽ በአስር እጥፍ ከኢትዮጵያ የሚበልጡ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች አሏት ። የተዋጊ ጀት ብዛት ብቻውን ግብጽን አሸናፊ እንደማያደርጋት ግን መንግስቷ በደንብ ተረድቷል። በኢትዮጵያውን ደም ውስጥ ያለው ራስን የመከላከል ፍላጎት እና ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸው ቀናኢነት ግብጾች በግብታዊነት የሃይል እርምጃ እንዳይወስዱና ቆም ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

ግብጾች እጅ እየሰጡ መምጣታቸውንና እራሳቸውን ከእውነታው ጋር እያስታረቁ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው። የአገሪቱ ፓርላማ በህዳሴ ግድብ የተነሳ ሊደርስ የሚችለውን የውሃ መቀነስ ለመከላከል አዲስ ህግ እያረቀቀ ነው። ህጉ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ህጉ ግብጾች ውሃን እንደ ድሮው በፈለጉት መንገድ መጠቀም እንደማይችሉ ለመቆጣጠር ተብሎ የተዘጋጀ ነው። አዲሱ ህግ ህዝቡ የውሃ አጠቃቀም ባህሪውን እንዲለውጥ ያዛል። ከፍተኛ ውሃ በሚጠቀሙ እንደ ሩዝ በመሳሰሉ እርሻዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግም ያሳስባል። በከተሞች ውስጥ ለመንገድ ጽዳትና ለመኪና ማጠቢያ በሚል ውሃ መድፋት በህግ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። ህጉ ጥብቅ መሆኑና የውሃ ድህነት እንዲህ አይነት ጠንካራ ህግ እንዲያወጡ እያሰገደዳቸው መሆኑን ህጉን የሚያረቁት የፓርላማ አባላት ይናገራሉ።

የአገሪቱ ዜጎች ግን መንግስት በድርደሩ ሲሸነፍ እንዲህ አይነት ህግ ለማውጣት መገደዱን በማንሳት እየተቹት ነው። የተሻለ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት ማበጀት ተገቢ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ተጽዕኖ መፍጠር ይገባ ነበር በማለት የግብጽ ምሁራን እንደሚናገሩ አል ሞኒተር የተባለው የግብጽ ሚዲያ ባወጣው ሰፊ ዘገባ ገልጿል።

ግብጾች ከእውነታው ጋር ለመኖር መድፈር እንዳለባቸው ባለስልጣናቱ ማሳሰብ መጀመራቸው ለኢትዮጵያ መልካም ዜና ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የያዘው አቋምም ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: