ኢትዮጵያ የነዳጅ አምራች አገራትን ልትቀላቀል ነው

( ERF) ኢትዮጵያ ከብዙ አስር አመታት በሁዋላ የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራትን ልትቀላቀል ተቃርባለች። የአባይ ገድብ በሰላም ተጠናቆ ስራ ሲጀምርና ነዳጅ የማውጣቱና የመላኩ ስራ በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ፣ አገርቱ ሰፊ የኢነርጂ ገበያ ይኖራታል።

( ERF) አጼ ሃይለስላሴ እና ዲፕሎማቶቻቸው እነ አቶ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ ጆን ስፔንሰር፣ ብላታ ኤፍሬምና ሌሎቹም ኦጋዴንን ከእንግሊዝ እጅ ለማስጣል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርተዋል። የጣሊያንን ወራሪ ሃይል ለመውጋት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የእንግሊዝ ጦር ኦጋዴንን ለመልቀቅ ፍላጎት አልነበረውም። እንግሊዞች ኦጋዴንን ከሶማሊያ ጋር አቀላቅለው ታላቋን ሶማሊያ በመፍጠር የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ህልማቸውን እውን የማድረግ ምኞት ነበራቸው። ይህን ያውቁ የነበሩት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ከእንግሊዞች ጋር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሾች ተፋልመዋቸዋል። ኦጋዴንና ኤርትራ የቆዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች እንደነበሩ ሞግተዋቸዋል። ኤርትራንም ኦጋዴንንም እንደሚያጡ የተረዱት እንግሊዞች፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ የነበረው ሃብት ዘርፈው ከመውሰዳቸው በተጨማሪ ለአካባቢው ዘላለማዊ ፈንጅ ተክለው ሄደዋል።

እንግሊዞች አካባቢውን ለቀው ሲወጡ ኢትዮጵያ ወዲያውኑ ሲንክሊየር የተባለውን የአሜሪካ የነዳጅ ኩባንያ በማስመጣት የነዳጅ ፍለጋ እንዲካሄድ ፈቃድ ብትሰጥም፣ ኩባንያው ለገበያ የሚበቃ በቂ ምርት የለውም በሚል ፍለጋውን አቋርጦ ወጥቷል። የአሜሪካው ኩባንያ በወቅቱ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ይህ ነው የሚባል ፍለጋ አላካሄደም ነበር። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ወዳጅነት በወቅቱ ፖለቲካ የተነሳ ሲቋረጥና የአጼ ሃይለስላሴን መንግስት የተካው የደርግ መንግስት ወዳጅነቱን ከሩስያ ጋር ሲያጠነክር የሩስያ የነዳጅ ኩባንያ በኦጋዴን በኩል የነዳጅ ፍለጋ ስራ ውል ተዋዋለ። ይሁን እንጅ በጊዜው በውል ባልታወቀ ምክንያት ኩባንያውም ነዳጅ ማውጣት ሳይችል ቀረ።

ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በሁዋላ፣ የተለያዩ ኩባንያዎችን ወደ አካባቢው በመላክ የነዳጅ ፍለጋ እንዲያደርጉ ቢያደርግም፣ አንዳንዶች በቂ ነዳጅ የለም ሌሎች ደግሞ የጸጥታው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው በሚል ምክንያት ስራውን እያቋረጡ ሄደዋል። ይሁን እንጅ የቻይናው ፖሊ ጂ ሲ ኤል የተባለው ኩባንያ ላላፉት 6 ዓመታት ፍለጋውን አጠናክሮ በመቀጠል በቅርቡ የነዳጅ ማውጣት ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጥበቃል።

የቻይናው ኩባንያ በተፈጥሮ ጋዝና ዘይት ፍለጋ ላይ ተሰማርቶ ውጤት በማግኘቱ ፣ 760 ኪ ሜ የሚደርስ ከኦጋዴን ጅቡቲ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ በመዘርጋት ላይ ነው። ኩባንያው 4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመደበለት በካሉብ እና ሂላላ ፕሮጀክቱ ከ 3900 በርሚል ያላነስ የተፈጥሮ ጋዝ ለገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ እስከ 1 ሚሊዮን በርሜል የሚደርስ ክምችት አለው።

ከተፈጥሮ ጋዙ የኢትዮጵያ ድርሻ  በትክክል ምን ያክል እንደሆነ አይታወቅም። የአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዝኛው ክፍል የኢትዮጵያ ድርሻ ግማሽ ያክል ነው ቢልም ሌሎች መረጃዎች ግን  15 በመቶ ብቻ እንደሆነ ያሳያሉ።   የኮንትራት ስምምነት እኤአ በ2013 ሲፈረም የኢትዮጵያ ድርሻ 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ በወቅቱ የታተሙ ጋዜጦች ጽፈዋል።

ኩባንያው በዚህ አመት 3 ሚሊዮን ቶን የተፈጥሮ ጋዝ ለገበያ የማቅረብ እቅድ ሲኖረው፣ በእያመቱ እስከ 10 ሚሊዮን ቶን የመሸጥ እቅድ አለው። ቻይና የተፈጥሮ ጋዙ ዋነኛ መዳረሻ ትሆናለች ።

የተፈጥሮ ጋዙ ከሰልፈር ነጻ የሆነና በየትኛውም መስፈርት ከአለም ምርጥ የሚባል ነው። ይሁን እንጅ የአካባቢው አርብቶ አደሮች በኩባንያው የተነሳ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ኢኦኤ እንደዘገበው ኩባንያው ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ 2ሺ ያላነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ባለታወቀ በሽታ ህይወታቸው አልፏል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከኩባንያው ስራ ጋር በተያያዘ የተከሰተ በሽታ እንደሌለ ያስተባብላል።

ኢትዮጵያ በዚህ አመት የነዳጅ አምራች አገራትን ትቀላቀላለች ። ከነዳጅ የሚገኘው ገንዘብ በአገባቡ ትቅም ላይ ከዋለ ድህነትን ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: