የፋኖና የአማራ ክልል መንግስት ፍጥጫ

ሪፓርታዥ

( ERF) በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ የህወሃትን መንግስት በዱር በገደሉ ሲዋጉ የነበሩ ታጋዮች አንዳንዶች ትጥቃቸውን እያስረከቡ ሌሎች ደግሞ እስከነ ትጥቃቸው ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ተቀላቀሉ። ኤርትራ የነበሩት እንደ ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት7 እና አዴሃን የመሳሰሉ “ነጻ አውጪዎች” ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ በድል አድራጊነት መንፈስ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሌሎች በአገር ውስጥ ሆነው ሲደራጁ የነበሩት፣ በተለይ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩትን ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን ለመያዝ ከተላከው የህወሃት/አህአዴግ ሰራዊት ጋር ተፋልመው ጫካ የገቡ በርካታ የጎንደርና አካባቢዋ ተወላጆችም እንዲሁ የጀግና አቀባባል ተደርጎላቸዋል።

ከኤርትራ ከተመለሱትና በአገር ውስጥ ከነበሩት ታጋዮች መካከል የተወሰኑት ራሳቸውን ፋኖ በሚል ስያሜ በመጥራት አንዳንድ የፖለቲካ ትግሎችን ሲያካሄዱ ቆይተዋል። በተለይ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ፣ በከምሴ ከኦነግ ጋር በተደረገው ውጊያ እንዲሁም በትግራይ ድንበር አካባቢ በመንቀሳቀስ ሰላም የማስከበር ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ አንዳንዶች ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር እየተናበቡ ሰላም የማስከበር ስራ ሲሰሩ ቢሰሩም፣ አንዳንዶች ግን በተቃራኒው የክልሉን ሰላም የሚያደፍረስ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። በግልጽ ከባለሃብቶች ገንዘብ መጠየቅና ገንዘብ በማይሰጡት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ በምሽት በመጠጥ ሃይል እየተደፋፈሩ ተኩስ በመተኮስ የህዝብን ሰላም እስከማናጋት የደረሱ የፋኖ አባላት አሉ። እንዲህ አይነቱ ድርጊት እያሳሳበው የመጣው የአማራ ክልል መንግስት፣ በጊዜው የጸጥታውን ስራ ይሰሩ ለነበሩት ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ አንድ የቤት ስራ ሰጣቸው። የቤት ስራውም ፋኖ ወደ መንግስት ልዩ ሃይል የሚካተትበትን መንገድ እንዲፈልጉ ካልሆነም፣ ትጥቅ እንዲፈቱ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነበር። ብ/ጄ አሳምነው የፋኖ ኢ መደበኛ አደረጃጀት ጸጥታን ለማስጠበቅ እንደሚጠቅም፣ በመንግስት ስር ይሁኑ ቢባል ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል በማስጠንቀቅ፣ ፋኖ ራሱን የቻለ አደረጃጀት ኖሮት እንዲወጣና ከመንግስት ጋር እየተባበረ ስራ እንዲሰራ እንዲደረግ ሃሳብ አቀረቡ። በፋኖ ስር ተደራጅተው ወንጀል የሚፈጽሙትን ግን እንደማይምሩዋቸው አሳወቁ።

የወቅቱ የአዴፓ አመራሮች በበኩላቸው፣ የጦር መሳሪያ የመያዝና ጸጥታ የማስጠበቅ ስራ በህግ ለመንግስት ብቻ የተሰጠ ስልጣን መሆኑን በማስታወስ፣ ፋኖ ጸጥታ አስከብራለሁ ካለ አመራሩ በመንግስት ስር መሆን አለበት የሚል አቋም ያዙ። በዚህ ጉዳይ በጄ/ል አሳምነውና በ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም እሳቸውን በተኩዋቸው ዶ/ር አምባቸው መኮንን መካከል ልዩነት ተፈጠረ። አንዳንድ የፋኖ አባላትም በወንጀል ድርጊት መቀጠላቸው ስጋት ላይ የጣላቸው የክልሉ ባለሃብቶችና ነዋሪዎች መንግስት እርምጃ እንዲወስድላቸው ግፊት ማድረግ ጀመሩ። መንግስትም የፋኖ አባላት ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ካልሆነም በመንግስት ስር እንዲሆኑ ሽምግልና ያዘ። የፋኖ አባላቱ ግን በራሳቸው መደራጀታቸው ክልሉን እንደሚጠቅም፣ ከሁሉም በላይ በወልቃይት ጉዳይ ከህወሃት ጋር ያልተጠናቀቀ ትግል እንደሚጠብቃቸው በመግለጽ ትጥቃቸውን እንደማይፈቱ በመንግስትም ስር እንደማይሆኑ አቋማቸው ግልጽ አደረጉ ። ሁኔታው በክልሉ ውስጥ ሁለት መንግስትን ፈጠረ። የፋኖ መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ጸጥታ የማስከበር ስራ የመጀመሪያ ተግባሩ እንዲሆን ጠንካራ ውሳኔ አሳለፈ። ፓርቲው ኢላማ ያደረገውም በኦሮምያ ክልል በኦነግ፣ በአማራ ክልል ደግሞ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ነው። እነዚህ ኢ መደበኛ አደረጃጀቶች ወደ መደበኛው የመንግስት አደረጃጀት እንዲገቡ ካልሆነም ትጥቅ እንዲፈቱ ፓርቲው ጥብቅ መመሪያ አስተላለፈ። በዚህ ውሳኔ መሰረት የኦሮምያ ክልል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር በኦነግ ሃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ወሰደ። የአማራ ክልል ግን የፋኖ ሃይሎች በይፋ ጦርነት ያላወጁ በመሆኑ እንደ ኦሮምያ ክልል መከላከያውን ጋብዞ እርምጃ ለመውሰድ ተቸገረ። የአካባቢውን ሰላም ይበልጥ ላለማናጋት በሚል መታገስንና ሰላማዊን አማራጭን መከተል መረጠ። ይሁን እጅ ቀን በገፋ ቁጥር በመንግስትና በፋኖ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እየሻከረ ሄደ። አንዳድ የፋኖ አባላት በአደባባይ የሚሰጡት መግለጫም የፌደራል መንግስቱን እያሳሰበ ሄደ። ከሁሉም በላይ የፌደራል መንግስቱን የኦነግ ተቀጽላ እንደሆነ ተደርጎ በፋኖ አመራሮች የሚሰራጨው ወሬ የክልሉን ባለስልጣናት ከፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ጋር እያለያያቸው ሄደ።

የክልሉ የጸጥታ ቢሮ  ፋኖ ወደ መደበኛው የመንግስት አደረጃጀት የማይገባ ከሆነ በክልሉ የእርስ በርስ ጦርነት ሊጀመር እንደሚችል በመግለጽ፣ በፋኖ ላይ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ። ይህም ሲሆን ግን ችግሩን በራሱ ለመወጣት እንጅ መከላከያን ለመጋበዝ አልፈለገም። ክልሉ በቅርቡ ባጠናው አንድ ጥናት ላይ ፋኖን በተመለከተ የገጠመውን ፈተናና የሚወስደውን እርምጃ እንዲህ ሲል አስፍሯል ፡

 “ በክልሉ ውስጥ የተፈጠሩ ኢ መደበኛ አደረጃጀቶች በፍጥነት መልክ ካልያዙ፣ አማራ ክልል እንኳንስ የውጭ ጠላቶቹን በብቃት ሊመክት ይቅርና እርስ በርስ የሚጠፋፋበት ክልል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ካሁን ቀደምም ዋጋ ከፍለንበታል( የሰኔ 15ን ማለቱ ነው)። ፋኖ ከአሁን ቀደም በአማራ ክልል ላይ ይደርስ የነበረውን በደል በውል በመረዳት ከፍተኛ ትግል ያደረገ አደረጃጀት እንደነበር ቢታወቅም፣ ለከፈሉት ከፍተኛ መስዋትነት እውቅና ከመስጠት ውጪ ከመንግስት እዝ ውጭ በመሆን እንደበፊቱ የመንግስትን ስራ ተክተው መስራት እንደማይችሉ መታወቅ አለበት ። ስለሆነም በክልላችን የተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ታቅፈው በመንግስት እዝ ስር ሆነው የሚቀጥሉበት ሁኔታ በፍጥነት መሰራት አለበት ። በዚህ አማራጭ የማይታቀፍ የፋኖ አመራር እና አባል ካለ ወደመደበኛ  የግል ስራው ማተኮር ይኖርበታል።  ህግ የማስከበር ስራ የመንግስት ተግባር እንጅ የማንም አለመሆኑን መታወቅ አለበት ። ህዝብ አጋዥና ተባባሪ ነው። ይህን የማናደርግ ከሆነና የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ በዚህ አይነት ቀጥሎ የዜጎች ህይወት በከንቱ እየተቀጠፈ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ ፍትህ በጉልበተኞች እጅ ስትወደቅ ዝም ብሎ የሚመለከት መንግስት ሊኖር አይገባውም። ምርጫችን አንድ ብቻ ነው። የሚከፈለው መስዋትነት ተከፍሎ  የክልላችንን የህግ የበላይነት ማረጋገጥ። ካልቻልን ስልጣን ለማስረከብ መወሰን ይኖርብናል።”

ከቅርቡ ጊዜ ወዲህ በፋኖ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ይህን ጥናት ተከትሎ የመጣ ነው። ፋኖና የአማራ ክልል መንግስት ልዩነታቸውን በሰላም መፍታት ቢችሉ፤ ፋኖ ህግን የማስከበር ስራ የመንግስት ብቻ መሆኑን አውቆ በመንግስት ልዩ ሃይል ስር ቢጠቃለል፤ ካልሆነም ለፋኖ አመራሮች የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ወደ ግል ስራ ወይም ወደ መንግስት ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ችግሩን ደም ሳይፈስ መፍታት እንደሚቻል ምክራቸውን የሚለግሱ ብዙዎች ናቸው።

http://www.ethio-redfox.com

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: