ገዱ አንዳርጋቸው ትክክለኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው ?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ተወዳጅ ነበሩ። ታጋሽ፣ አድማጭ፣ ነገሮችን ከሩቅ ማሽተት የሚችሉ፣ ተግባቢና በሳል ሰው እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። እርሳቸው ክልሉን ሲመሩ በነበረበት ወቅት ከህወሃት ይደርስባቸው የነበረውን ተደጋጋሚ ጫና ተቋቁመው፣ የህወሃት አገዛዝ እንዲወገድ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል። ከኦህዴድ ጋር ሚስጢራዊ ግንኙነት  በመመስረትም፣ ህወሃት አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት እና ስልጣን ላይ ለመቆየት ያደረግ የነበረውን ሙከራ አክሽፈዋል። በአጠቃላይ የለውጡ ሞተር ከሆኑት ጥቂት ሰዎች ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው።

አቶ ገዱ የአማራ ክልል መሪነትን በጫና በተለይም በእነ ጄ/ል አሳምነው ግፊት እንዲለቁ ከተደረጉ በሁዋላ የት ቦታ ይመደቡ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ነበር። በነገራችን ላይ አቶ ገዱ በክልል ፕሬዚዳንትነት የቆዩት ያለፍላጎታቸው ነበር፤ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም፣ ድርጅታቸው እርሳቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ አልነበረም። ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ክልሉን ከህወሃት እና ከኦነግ ጥቃት ለመከላከል የረዳሉ በሚል እምነት ከተሾሙ በሁዋላ፣ ይውሰዱዋቸው የነበሩት እርምጃዎች እነ አቶ ገዱን የሚያስደስቱ አለነበሩም። አቶ ገዱና ጓደኞቻቸው የብሄር ፖለቲካ ኢትዮጵያን እየጎዳ መሆኑን በመረዳት፣ ኢትዮጵያ በሄደት ከዚህ አይነቱ ፖለቲካ መውጣት አለባት የሚል እምነት ነበራቸው። የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይ ብሄርተኝነት እንዲለዝብ እና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከፍ እንዲል ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ የመጣው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንዲለዝብ ከአቶ ለማና ዶ/ር አብይ ጋር የተለያዩ እቅዶችን እያወጡ ለመተግበር በሚሯሯጡበት ወቅት፣ ጄ/ል አሳምነውና በዙሪያቸው ያሰለፏቸው የአማራ አክቲቪስቶች በተቃራኒው የአማራ ብሄርተኝነት ከፍ እንዲል የተለያዩ የቅስቀሳ ሰራዎችን ይሰሩ ነበር። ኦነግ በከምሴና በሰሜን ሸዋ አካባቢ ያደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ለእነ አሳምነውና ለአማራ አክቲቪስቶች፣ የአማራ ብሄርተኝነትን ከፍ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸው ነበር። እነ አቶ ገዱና አቶ ለማ ኦነግ እረጅም እርቀት እንደማይሄድና በሂደት ተመትቶ እንደሚወድቅ ያምኑ ስለነበር፣ የኦነግ ጉዳዩ ተጋኖ እንዳይቀርብ ፍላጎት ነበራቸው።

አቶ ገዱ ከእነ አቶ ለማና ዶ/ር አብይ ጋር በነበራቸው የተጠበቀ ወዳጅነት የተነሳ በእነ ጄ/ል አሳምነው ወገን በጥርጣሬ እየታዩ ይተቹ ነበር። አቶ ገዱ የኦነግ ( የአብይ ተላላኪ ) ነው በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ዘመቻ እንዲከፈትባቸው ያስደረጉትም እነ ጄ/ል አሳምነው ነበሩ። በአማራ ብሄርተኞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ የመጡት የክልሉን ደህንነት ሲመሩ የነበሩት ጄ/ል አሳምነው፣ አቶ ገዱ ከክልል ስልጣን እንዲነሱና በዶ/ር አምባቸው መኮንን እንዲተኩ ከፍተኛ ግፊት አድርገው ተሳክቶላቸዋል። ዶ/ር አምባቸውም ወጀቡ ስቧቸው ክልሉን ለመምራት ከፍተኛ ፍላጎት በማሳደራቸው፣አቶ ገዱ ክልሉን “አያሳየኝ” ብለው ወደ ፌደራል ሄደዋል።

አቶ ገዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ አንዳንድ ወገኖች መስሪያ ቤቱ የእርሳቸው ትክክለኛ ቦታ እንዳልሆነ ይገልጹ ነበር። ብዙዎቹ በምክንያትነት የሚያነሱት ደግሞ የቋንቋ ጉዳይ ነበር። አቶ ገዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በሁዋላ በርካታ አወንታዊ ስራዎችን ሰርተዋል። በዚህም መመስገን ይገባቸዋል። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ከዚህ በሁዋላ የሚጠብቃትን በተለይ ከሃዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚገጥማትን ፈተና ለመቋቋም፣ ከአቶ ገዱ የተሻለ ዲፕሎማት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንደምትገኝ መካድ አይቻልም። አቶ ገዱ ከባህሪያቸውም ሆነ ከልምዳቸው አንጻር ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ይልቅ፣ የደህንነት ወይም የሰላም ሚኒስትርነቱን ስልጣን ቢይዙ የተዋጣለት ስራ እንደሚሰሩ እርሳቸውን የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ። ወ/ሮ ሙፈርያትም በሰላም ሚኒስትርነታቸው ጥሩ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። እርሳቸው በቦታቸው ላይ ይቆዩ ቢባል እንኳን፣ አቶ ገዱን በሌሎች ከህዝብ ጋር በቀጥታ በሚያገናኛቸው ከፍተኛ የሹመት ቦታ ላይ ሊመደቡ ይገባል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መመራት ያላበት የዲፕሎማሲ ልምድ ባለው፣ የአለማቀፍ ግንኙነትና የአለማቀፍ ህግ ትምህርት በወሰደ እንዲሁም እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ በጥራት በሚናገር ሰው መሆን አለበት ። ኢትዮጵያ ከአባይ ጋር ተያይዞ ሊገጥማት የሚችለውን የዲፕሎማሲ ጦርነት ማሽነፍ የሚቻለው እንዲህ አይነት ሰው በሚኒስትርነት መሾም ሲቻል ብቻ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጠራ እንግሊዝኛ በአለማቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየቀረበ የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ እንዲሁም ከተለያዩ ዲፕሎማቶች ጋር እየተገናኘ አገሮች ኢትዮጵያን ደግፈው እንዲቆሙ የማሳመን ስራ የሚሰራ መሆን አለበት። እንዲህ አይነቱን ሰው ከብልጽግ ፓርቲ ውስጥ ማግኘት ባይቻል እንኳን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ሲሰሩ ከነበሩ ዲፕሎማቶች ወይም ከምሁራን መካከል መርጦ መሾም ይቻላል።

ይህን የምልበት ዋናው ምክንያት ግብጽ የአባይን ጉዳይ ወደ አፍሪካ ህብረት እና ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ እየተዘጋጀች መሆኗን የአገሪቱ ፖለቲከኞች እየገለጹ መሆኑን ስለተረዳሁ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ በዲፕሎማሲው ረገድ የሚገጥመን ፈተና ቀላል አይሆንም ማለት ነው። በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ወይም በተባባሩት መንግስታት ድርጅት ሜዳ ላይ በአማርኛ ወይም ጥራት በሌለው እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ ተከራክረን ልናሸንፍ አንችልም። ሃሳብና እውቀት ብቻ ሳይሆን የቋንቋን ችሎታም ለአሸናፊነትን እንደሚያበቃ መረሳት የለበትም።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እየመጣ ያለውን ፈተና አውቀው በጊዜ ሊዘጋጁ ይገባል።ይህ የፓርቲ ወይም የብሄር ጉዳይ አይደለም። ይህ አቶ ገዱን በመጥላት ወይም ዝቅ ለማድረግ የተሰጠ አስተያየት አይደለም። ይህ ጸሃፊ ለአቶ ገዱ ያለው አክብሮት እጅግ የላቀ ነው። እርሳቸው ከፍተኛ የስልጣን ቦታ ላይ መመደብ እንዳለባቸውም በጽኑ ያምናል። በተለይ የአገሪቱን ደህንነት በበላይነት ቢመሩ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። አስተያየቱ የምሰጠው ኢትዮጵያን በመውደድና ከአባይ ጋር የሚገጥሙንን የዲፕሎማሲ ጦርነቶች በአሸናፊ ለመወጣት ካለኝ ምኞት አንጻር ነው። ጠ/ሚ አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ከፓርቲ በላይ መሆኗን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ይህን እምነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩን እንጠብቃለን። አደራ የምለው ግን አቶ ገዱን አንስተው እንደ ወርቅነህ ገበየሁ አይነቱን ሰው ሾመው አገራችንን ከሁለት ያጣ ጎመን እንዳያደርጓት ነው።

ሳሙኤል ሰይፉ

http://www.ethio-redfox.com

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: