እምነትን ፈተና ላይ የጣለው ኮሮና

የሰው ልጅ እምነት ወይም ሃይማኖት የሚፈተነው አደገኛ በሽታ ሲከሰት ነው። አንዳንዱ እኔ የማመልከው ፈጣሪ ያድነኛል ብሎ ሙሉ እምነቱን ወደ ፈጣሪው ያደርጋል። ሌላው ደግሞ  ሳይንስ የሚለውን መከተል ይመርጣል። እንደ ኮሮና ቫይረስ አይነት አደገኛ ወረርሽኝ ሲመጣ ሰዎች “ ወደ ክሊኒክ ልሂድ ወይስ ወደ ቤተ ክርስቲያን?” በሚል እምነትን በሚፈታተን ጥያቄ ይወጠራሉ። በአውሮፓ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እየተው ሳይንስን መከተል የጀመሩት በአብዛኛው ከበሽታ ጋር በተያያዘ ነው። በጸሎት ያልዳኑ በሽታዎች በሳይንሳዊ መንገድ መዳን ሲጀምሩ ሰዎች የሃይማኖትን ጉልበት እየተጠራጠሩ፣ የሳይንስን ጉልበት እያመኑ እንዲሄዱ ጥናቶች ያሳያሉ።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ዛሬ ላይ የምንታዘበው ሃይማኖት በሳይንስ የተነሳ ዳግም ፈተና ውስጥ የወደቀ መምጣቱን ነው። በእስልምናም ሆነ በክርስትና ሃይማኖቶች ከፈጣሪ የበለጠ አዳኝ ወይም ፈዋሽ የለም። ማንኛውም አይነት በሽታ በጸሎት እንደሚድን ሁለቱም ሃይማኖቶች ይሰብካሉ። ይሁን እንጅ እንደ ኮሮና አይነት በሽታ ሲመጣ፣ ሃይማኖቶቹ ቀደም ብለው ሲሰብኩ የቆዩትን ይረሱና ህዝቡ ሳይንሱን እንዲከተል ይመክራሉ። “ጸሎት ብቻውን ይፈውሳችኋልና፣ ሳይንሱን አትከተሉ” ብለው በድፍረት መናገር አይችሉም። ሰይጣንን በካልቾ እየመቱ ሰዎችን “ሲፈውሱ” የሚያሳዩት ፓስተሮች እንኳን፣ ወረርሽኝ ሲመጣ ቤተክርስቲያናቸውን ዘግተው ይመሽጋሉ። በእስልምና ያለውም ከዚህ የተለዬ አይደለም።

አርብ ( ጁመዓ) የሙስሊም ማህበረሰብ ሰብሰብ ብሎ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበትና የሚለምንበት የተቀደሰ ቀን ነው። ይሁን እንጅ የስልምና ማዕከል ከሆነችው ሳውድ አረቢያ ጀምሮ እስከ ኢንዶኒዥያ ያሉ መስጊዶች በሙሉ ተዘግተው ውለዋል። ለዛሬ ቀን ብቻ የተከፈቱት የመካና የመዲና 2ቱ ታላላቅ መስኪዶች እንኳን ኢማሞች እስከሚደነግጡ ድረስ በሰው ድርቅ ተመተው ውለዋል። ከፓኪስታንና ከሞቃዲሾ በስተቀር በመላው አለም የሚገኙ እጅግ አብዛኞቹ መስኪዶች ተዘግተው ሙስሊሙ በቤቱ ድዋ ሲያደርግ ውሏል። ሙስሊሙ የወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ በሳይንስ አንጻር ከታየ ትክክል ነው። አብዛኛው ህዝብም በጭንቅ ጊዜ ፊቱን ወደ ሳይንስ ማዞሩ ሁሌም የሚታይ እውነታ ነው። ችግሩ ግን ጤና በተገኘ ጊዜ ሃይማኖተኞች ሁሉንም ረስተው ሳይንስን መልሰው የሚያንቋሽሹ መሆናቸው ነው።

ቫቲካንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያኖችም ደጃቸውን ዘግተዋል። የስናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት እንደጠፋ የሚያሳይ ክስተት ነው። ህዝብ በሽታን ለመከላከል ሳይንሳዊ መንገዶችን እየተከተለ መምጣቱ ትክክል ነው። ሃይማኖቶችም ህዝቡ እንዲህ አይነቱን መንገድ እንዲከተል መምከራቸው ትክክል ናቸው። የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች እንደ ኮሮና ቫይረስ አይነት በሽታዎችን ለመከላከል ሁሌም ፊታቸውን ወደ ሳይንስ ማዞር አለባቸው። በሽታው የያዛቸው ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ወይም ወደ ጸበል ቦታ ወይም ወደ ቃሊቻ በመሄድ እንደማይፈወሱ ሊገነዘቡ ይገባል፤ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ከማባከን ውጭ የድነት ትርፍ አያገኙም። እንዲያውም በሽታው እንዲስፋፋ ስለሚያደርጉ በአገር ላይ የበለጠ ጉዳት ያደርሳሉ። ፈውስ እንሰጣለን የሚሉ የሃማኖት አባቶችም አጉል ተሰፋ እየሰጡ ህዝቡ ሳይንሳዊ መንገዶችን እንዳይከተል ከሚያደርግ ድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው። ሃይማኖት የሚያገለግልበት ቦታ አለ፤ እንደ ኮሮና ቫይረስ የመሳሰሉትን በሽታዎች መከላከል የሚቻለው ግን በሳይንሳዊ ዘዴ ብቻ በመሆኑ ህዝቡ የሃኪሞችን ምክር ብቻ እንዲሰማ ሊያበረታቱ ይገባል። በውጭ አገራት የሚገኙ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች የወሰዱት የጥንቃቄ እርምጃ በኢትዮጵያም መተግበር ይገባዋል!

ሻፊ ከሱዳን

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: