ጎንደር ሌሊቱን በጥይት ድምጽ ስትረበሽ አደረች

( ERF) የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ፋኖ በሚል ስም በተለያዩ መንገዶች ተደራጅተው ዝርፊያ ይፈጽማሉ ባላቸው ታጣቂዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ፣ ከተማዋ ሌሊቱን በተኩስ ስትናወጥ አድራለች ። የከባድ መሳሪያ ድምጾች የሰሙ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ በተኩሱ ጉዳት የደረሰበት አካል ስለመኖሩ ግን እርግጠኞች መሆን አልቻሉም።

ፋኖን በተመለከተ የከተማው ህዝብ በሁለት ተከፍሏል። በፋኖ ስም የሚዘርፉና የከተማውን ህዝብ ሰላም የሚነሱ በአንድ በኩል፣ ትጥቃቸውን ያልፈቱ ነገር ግን ሰላማዊ የሆነ ኑሮ የሚኖሩ የፋኖ አባላት በሌላ በኩል አሉ። ህዝቡ በዘራፊ ፋኖዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድለት ሲጠይቅ ቆይቷል። በእነዚህ የተነሳ ግን የህዝብ አጋር ተደርገው በሚታዩት ፋኖዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው አይፈልግም ።

የፋኖ አባላት በበኩላቸው መንግስት በእርምጃው የሚቀጥል ከሆነ በመላው አማራ ተቃውሞ እናቀጣጥላለን፣ በ2008 ጎንደር ላይ የነበረውንም እንደግማለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ችግሩን ለመፍታትም የሽምግልና ጥረት ተጀምሯል። የክልሉ መንግስት ከዚህ በሁዋላ በኢ መደበኛ አደረጃጀት ሰላምን ማስከበር አይቻልም የሚል ውሳኔ አሳልፏል፤ ሁሉም ፋኖዎች ወደ መንግስት ሰራዊት እንዲገቡ ካለሆነም ወደ ግል ኑሮአቸው እንዲመለሱ መደረግ አለበት ብሏል። ፋኖዎች በበኩላቸው የአማራ ህዝብ በኦነግና በህወሃት ተከቦ ትጥቅ ፍቱ መባሉ ትክክል አይደለም በሚል ትጥቅ ለመፍታት ወይም አደረጃጀታቸውን ለመበተን ፈቃደኞች አይደሉም። ዋናዎቹ ፋኖዎች በስማቸው ዝርፊያ እንደሚፈጸም መረጃ ቢኖራቸውም ለማስቆም ግን አልቻሉም።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: