ለአብይ አህመድ 10 ዓመት ጀባ በሉት

አብይ አህመድ ራዕይ አለው። የመለስ ራዕይ እያልክ ስታደነቁረን የነበርክ ሁሉ፣ራዕይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከአብይ ተማር። ራዕይ ዙሪያን አይቶ፣ ዙሪያን ለመለወጥ መነሳት ነው። መለስ ዜናዊ 25 ዓመታት ቤተ መንግስት ተቀምጦ ያልታየውን ራዕይ፣ አብይ በ25 ሳምንታት ነፍስ ዘራበት፤ ቤተመንግስቱ ከአዜብ የቆሻሻ መጣያ ገንዳነት አልፎ፣ ሰው የሚጎበኘው ቦታ ሆነ። “አዲስ አበባ ያብባል” ገና የተባለው ትንቢት እውን ሊሆን ምንም አልቀረው። የሸገር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ አዲስ አበቤ የሚያወራውንና የሚሰራውን ሰው ለመለየት እድል ያገኛል። ኮሮና የሚባል ቫይረስ ባይመጣና እነዚህ ፕሮጀክቶች ያለ ገንዘብ ችግር ተፈጻሚ ሆነው ብናያቸው ኖሮ፣ እንዴት በታደልን ነበር። ግን ኮሮና እንዳያጨናግፋቸው እፈራለሁ።

ራዕይ የሚለው ስም ሲነሳ ፈጥኖ ወደ አዕምሮየ የሚመጣው መለስ ዜናዊ ነው። እድሜ ለበረከት ስምዕኦን፣ በህይወት ሲኖር ራዕይ አልባ የነበረን ሰው፣ ሲሞት ባለ ራዕይ አድርጎ በፕሮፓጋንዳ ብዛት ጭንቅላታችን ውስጥ ከተተው። የመለስ ራዕይ ምን ነበር ግን? ይህን ለመመለስ ብዙ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፤ መለስ ራዕዩ ስልጣን ነበር። ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው ሁሉም ነገር እሱን ስልጣን ላይ እንዲያቆየው ተደርጎ የሚቀረጽ ነበር። በቃ የመለስ ራዕይ ከእሱ ስልጣንና ያለፈ አልነበረም።

አብይ አህመድ በኢቢኤስ  የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ራዕዩን ሲያካፍል ስትሰማ፣ ራዕይ ማለት ምን እንደሆን ይገባሃል። ስለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጥቅም አብይ አህመድ ሲያብራራ ስትሰማ፣ የመለስን ዘመን እየረገምክ፣ ምንነው ይህ ሰው ቀድም ብሎ ስልጣን ይዞ በነበር ትላለህ።

አብይ እንደ ሰው ሊሳሳት ይችላል። ይሳሳታልም። ግን ለሃገሩ ግልጽ ራዕይ ያለው ዘመናዊ ሰው ነው። ኢሜል በወጉ ከፍተው መዝጋት ከማይችሉት የአገራችን ፖለቲከኞች ጋር የምታወዳድረው ሰው አይደለም። በብዙ እጅ መጥቆ ሄዷል። ውሎውና ጓደኝነቱ ከእነ ጃክ ማ ጋር ሲሆን፣ ምን አይነት ራዕይ ሊኖረው እንደሚችል የገባሃል ።

አብይ አህመድ በአለም በታወቁ ዩኒቨርስቲዎች ላይመረቅ ይችላል። ነገር ግን በንባብና በተፈጥሮ እውቀት ራሱን ከትቢያ አንስቶ ሰው ያደረገ ሰው ነው። በታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች ከተመረቁት የሚበልጥ እንጅ የሚያንስ እውቀት የለውም። ለዚህ ጥረቱ አክብሮት ሊሰጠው ይገባል።

አብይ ነጻ ምርጫ አድርጎ እንዲመረጥ ምኞቴ ነው። የዲሞክራሲን እውነተኛ ሃዲድ መስራት አለበት። ነጻ ምርጫ ቢደረግ፣ በግሌ የምመርጠው አብይን ነው። ራዕይ አለው፤ ራዕዩን እንዲያስፈጽም የእድሜየን 10 ዓመት የምስጠው ለአብይ ነው። አገሬን ለመሸታ ቤቱ ፖለቲከኛ አሳልፌ ሰጥቼ  የአረቂና የቢራ ፋብሪካ ማከማቻ እንድትሆን አልመኝም። በአገሬ ሲልከን ቫሊን ማየት የምችለው በአብይ ነው ። አብይ ራዕይ አለው። በአብይ ራዕይ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሪነት ስትገሰገስ ይታየኛል። አስር ዓመት ጀባ በሉት፣ እኔ ጀባ ብየዋለሁ።  

ሱራፌል ሽበሺ

ጀርመን

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: