የአባይን ግድብ ኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ችግር መሸፋኛ አድርጋዋለች ሲሉ የግብጹ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ተናገሩ

(ERF) ሙሃመድ አብደል አታይ DMC ከተባለ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ ኢትዮጵያ የውስጥ የፖለቲካ ችግሯን ለመሸፈን ስትል የአባይን ግድብ አጀንዳ አድርጋ ብዙ ቢሊዮን ዶላር እያፈሰሰች ነው” ብለዋል። “ብዙ ገንዘብ እያፈሰሱ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ነው የምንሰራው ይላሉ፣ እውነቱን ለመናገር ግድቡን በአነስተኛ ወጪ መስራት ይቻል ነበር” ሲሉ አክለዋል።ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ግድቡ አሁን የሚገኝበትን ደረጃ ዲዛይን መላክ ቢኖርባትም እስካሁን እንዳልላከች የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አለማቀፍ ስምምነቶችን መፈረም የማትፈልገው ግድቡን ያለምንም ተጽዕኖና ገደብ በራሷ ብቻ ለመፈጸም ስለምትፈልግ ነው ይላሉ።አባይ የሁሉም የጋራ ሃብት በመሆኑ፣ በግድቡ ዙሪያ ሁላችንም ስምምነት ላይ ልንደርስ ይገባል የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር የገባችበት ውዝግብ የመጀመሪያ እንዳልሆነና፣ ኬንያን ሳታማክር ሶስት ግድቦችን በመስራት ውዝግብ ውስጥ ገብታ ነበር ሲሉ ኢትዮጵያን በግብተኝነት ከሰዋታል። ሱዳን አሜሪካ ባቀረበችው የስምምነት ሃሳብ ብትስማማም ፊርማዋን አለማስቀመጧን አምነዋል። ግብጽ ለ 100 ዓመታት የውሃ ድርሻዋ ተጠብቆ መቆየቱንና ይህ ድርሻዋ እንዲቀንስባት እንደማትፈልግ ባለስልጣኑ አክለው ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ገዱ አንዳርጋቸው፣ ግብጽ እውነተኛ ፍትሃዊ የሆነ ድርድር እንደማትፈልግ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል አማራጭ ሃሳብ እየተዘጋጀ ነው። የኮሮና ቫይረስ የአለምን የሚዲያ ትኩረት ሙሉ በሙሉ ስቦ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት ግብጽና ኢትዮጵያ የአባይን ጉዳይ አሁን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገውታል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: