የኮሮና በሽታ ከአየር መንገድ ቀጥሎ በአበባ ገበያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው

(ERF) የኮሮና በሽታ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ ነው። ከአየር መንገድ ጋር በተያያዘ እስካሁን አገሪቱ ከ190 ሚሊዮን ዶላር በላይ አትጣለች። አሁን ደግሞ ሌላው የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው የአበባ እርሻው ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየተዘጋ ነው። ወደ ሆላንድ የሚላከው አበባ በመቋረጡ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የአበባ አምራች ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን ለማሰናበት ተገደዋል። በዚህም የተነሳ ከ 50 ሺ ያላነሱ ሰራተኞች ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል።

በጨርቃጨርቅና በጫማ ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎችም በተመሳሳይ መንገድ ስራ ለማቆም እየተገደዱ በመሆኑ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ስራቸውን ያጣሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በነዳጅ ዋጋ መቀነስና በወርቅ ዋጋ መጨመር መጠነኛ መረጋጋት ሊያሳይ ቢችልም፣ በአገልግሎቱ ዘርፍ፣ በተለይ ታላላቅ አለማቀፍ ስብሰባዎችን ተከትሎ ይገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሬ መቀነስ እንዲሁም በግንባታ ስራዎች ላይ የሚታየው መቀዛቀዝ ፣ ከነዳጅ ዋጋ መቀነስና ከወርቅ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ይገኝ የነበረውን ጥቅም አነስተኛ ያደርገዋል ።

ሌሎች የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ እንደ ጫት፣ ቡናና ሰሊጥን የመሳሰሉ ምርቶች ግብይት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

መንግስት ኮሮና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ( አይ ኤም ኤፍ) እና የአለም ባንክ በቅርቡ ለኢትዮጵያ 6 ቢሊዮን ዶላር፣ የአሜሪካ መንግስት ደግሞ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ገንዘቡ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ የሚረዳ ቢሆንም፣ የኮሮና ቫይረስ ተጽዕኖ አገሪቱን መልሶ ለውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይዳርጋት እና የዋጋ ንረቱንም እንዳያባብሰው ተሰግቷል።

በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኮሮና የሚያደርሰውን የኢኮኖሚ ጉዳት ለመቀነስ በጋራ ተደራጅተው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አንዳንድ አክቲቪስቶች ጥሪ እያቀረቡ ነው። በመጪው ሃምሌ ወር ውሃ መያዝ ይጀምራል የተባለው የህዳሴ ግድብ በገንዘብ እጥረት የተነሳ ስራው እንዳይስተጓጎል ኢትዮጵያውያን ልዩ ጥረት እንዲያደርጉ አክቲቪስቶች መክረዋል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: