አገር በፌስቡክና በሽፍታ አይመራም

የኢትዮጵያ ህዝብ በሶስት ሃይሎች እየተመራ ነው። አንደኛው መሪ መንግስት ነው። መንግስት ገና በህዝብ የተመረጠ ባይሆንም፣ በአጋጣሚ በያዘው ስልጣን አገር እየመራ ይገኛል። ከምርጫው በሁዋላ እውነተኛ መንግስት ይኖረናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሌላው አገር መሪ ደግሞ የጫካና የከተማ ሽፍታ ነው። በአገራችን በእያቅጣጫው ሽፍታ አገር እየዘረፈና ሰው እየገደለ ህዝብን እያማረረ ይገኛል። በጎንደር በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች፣ ህዝብን ቁምስቅሉን እያሳዩት ነው። ሰው ይገድላሉ፤ ገንዘብ አስገድደው ይቀበላሉ፤ሴት ይደፍራሉ፤የጠጡበትንና የበሉበትን አይከፍሉም፤ፖሊስ ጣቢያና የመንግስት ቢሮዎችን ይዘርፋሉ፤መሬት በህገ ወጥ መንገድ ይይዛሉ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ያወጣው መግለጫ፣ በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶች ምን ያክል ከተማዋን እንዳመሷት የሚያሳይ ነው። በኦሮምያ ያለው በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሰውም ሽፍታ ተመሳሳይ ድርጊት ይፈጽማል። የኦነግ ሽፍታ ሰው ገድሎ የሚያቃጥል፤ አባትና ልጅ በአንድ ቤት ውስጥ የሚረሽን ከአውሬ የባሰ ጨካኝ ነው። የዚህን አውሬ ባህሪ ታዬ ደንደአ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡

“ ወለጋ ላይ ከሸኔ የከፋ ኮሮና የለም።  ሸኔ በወለጋ ላይ ለመናገር የሚቀፍ ወንጀል ሲፈፅም ከርሟል። ብዙ ሰዎችን ያለምክንያት ገሏል። የበርካቶችን ሬሳ አቃጥሏል። ብዙዎችን አካለ ጎደሎ አድርጓል። አከባቢዉን በማቃወስ ሠላም እና ልማት እንዳይኖር አድርጓል። ሴቶችንና ወንዶችን ደፍሮ የዜጎችን ሞራል ሰብሯል። ሰዉ የራሱን ስጋ እንዲበላ አስገድዷል። ሰዉ የሚቀጠልበትን እንጨት ለቅሞ ተሰቅሎ ተቃጥሏል። ሴቶችንና ወንዶችን ጠልፎ ደብዛቸዉን አጥፍቷል።”

ሌላው አገር መሪ የፌስቡክ አክቲቪስቱ ነው። የኢትዮጵያ የፌስቡክ አክቲቪስቶች እንኳንስ አገር ሊመሩ እራሳቸውን እንኳን በወጉ ማስተዳደር የማይችሉ፤ የተወሰኑት ራስ ወዳድ፣ ስግብግብ፣  የአዕምሮ መቃወስ ያለባቸው፤ ከንባብ የተጣሉ እጅግ የሚያሳዝኑ ፍጥረቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች መጻፍና መናገር ስለቻሉ ብቻ የፌስቡክን ቴክኖሎጂ ለእኩይ አላማ እየተጠቀሙ ነው፤ ህዝብን በዘርና በሃይማኖት ለማጫረስ ሌት ተቀን እየደከሙ ነው። እነዚህን ከተፈጥሮና ከራሳቸው የተጣሉ ሰዎችን የሚከተሉዋቸው ብዙ የዋህና ያልበሰሉ ወጣቶች አሉ። አገሪቱ በእነዚህ ሰዎች የተነሳ ቁም ስቅሏል እያየች ነው።

መንግስት ኢትዮጵያን በአግባቡ መርቶ ወደ ዲሞክራሲና ልማት መውሰደ የሚችለው የፌስቡክ፣ የጫካና የከተማ ሽፍቶችን አደብ ማስገዛት ሲችል ነው። የፌስቡክ ሽፍታ ቃታ ስላልሳበ እንጅ ስራው ከጫካና እና ከከተማ ሽፍታ የሚተናነስ አይደለም። በሁሉም ላይ መንግስት ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድና ስርዓት ማስያዝ ይገባዋል። ከዚህ ውጭ መንግስትም አገሪቱን በአግባቡ ካልመራት ሽፍትነት ሊበራከት እንደሚችል ማወቅ አለበት።

የአማራ መማክርት ጉባኤ ፋኖን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ ተገቢና ወቅታዊ ነው። የኦሮሞ ምሁራንም በሸኔ ኦነግ ላይ ተመሳሳይ መግለጫ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። ሽፍትነት አገርን አይጠቅምም፤ በተለይ በአሁኑ ሰዓት የጦር መሳሪያ እንድናነሳ የሚያደርገን ሁኔታ የለም። ፖለቲካችን ሁሉ በሰላምና በሰላም ብቻ ሊካሄድ የገባዋል። መንግስት በዚህ ላይ አንድ አይኑን ጭፍኖ በቸልታ ሊያይ አይገባውም።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: