የዶ/ር አብይ ካቢኔ ኮሮናን ለመከላከል በቂ ስራ እየሰራ ነውን?

( ERF) የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት በአንዳንድ ወገኖች ሲያስመሰግነው በሌሎች ዘንድ ደግሞ እያስተቸው ነው።  በዚህ አጭር ጽሁፋ የዶ/ር አብይ መንግስት እስካሁን የወሰዳቸውን እርምጃዎች እንገመግማለን።

መንግስት ኮሮናን ለመከላከል ስራዎችን የጀመረው ዘግይቶ ነው። እንዲያውም ብልጽግና ፓርቲ ከ 1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር በላይ ከሰበሰበ በሁዋላ ነበር መንግስት ትኩረቱን ኮሮና ላይ ያደረገው። ከዚህም በሁዋላ ቢሆን፣ ፓርቲው ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን እያደረገ፣ ህዝቡን ለአደጋ አጋልጦት ቆይቷል።

ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ቻይና በኮሮና ተወጥራ በነበረበት ወቅት፣ ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት ሊዛመት እንደሚችል ተረድቶ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ሲገባው አላደረገም ። ለኮሮና መዛመት አንዱ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት በረራ እንዲያቆም ማድረግ ሲገባ ይህም አልተደረገም። በአጭሩ የመንግስት ቸልተኝነት ህዝቡን በቀላሉ በኮሮና ቫይረስ እንዲያዝ ሊያደርገው ይችል ነበር፤ ወይም አድርጎትም ሊሆን ይችላል።

መንግስት ዘግይቶ የወሰዳቸው እርምጃዎች ግን ከሞላ ጎደል ጥሩ የሚባሉ ናቸው። ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ በሽታውን በቀላሉ ከልጆች ወደ ወላጆች እንዳይዛመት ረድቷል። የሃይማኖት ተቋማት አንዳንድ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ለማግባባት ያደረገው ጥረትም፣ በከፊል ውጤት አስገኝቷል። የሃይማኖት ተቋማቷ የራሳቸው ችግር እንዳለ ሆኖ መንግስት ሃላፊነቱን ለመወጣት ያደረገው ጥረት የሚመሰገን ነው። አሁንም ግን ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ከካምፕ እንዳይወጣ፤ በሂደትም ሁሉም ድንበሮች እንዲዘጉ መወሰኑ አበጀህ የሚያስብል ነው። በትራንስፖርት ዘርፍ በኩል የተወሰደው እርምጃም ተገቢ ቢሆንም፣ በቂ ግን አይደለም። ይህን ችግር ለመፍታት  የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን ቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ የተወሰነውም ውሳኔ፣ ችግሩን ያን ያክል የሚቀርፈው ባይሆንም መልካም የሚባል ነው።

እስረኞች እንደ ወንጀላቸው መጠን እየታየ እንዲፈቱ መወሰኑም ተገቢ እርምጃ ነው። አፈጻጸሙ ግን አሁንም ዘግይቷል።

ዩኒቨርስቲዎች እንደተዘጉ ተማሪዎችን በፍጥነት ወደ ቤተሰቦቻቸው መላክ ተገቢ ይሆን ነበር። ዘግይቶም ቢሆን ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመላክ የተወሰነው ውሳኔ ከምንም ይሻላል።

ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ የሚደረገው ክትትል እና እየተወሰደ ያለው እርምጃ በጣም ጥሩና ተገቢ ነው። አርሶ አደሩን በተመለከተ እየተሰራ ያለው ስራ ግን ግልጽ አይደለም ወይም ትኩረት አልተሰጠውም።

በተለያዩ ፋብሪካዎች የሚሰሩ ሰራተኞችን በተመለከተ እስካሁን የተወሰደ እርምጃ የለም። ሁሉንም ነገር ለባለሃብቶች የመተው አዝማሚያ ይታያል። ይህ ትክክል አይደለም።

ከኮሮና ጋር የሚደርሰውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም፣ ዶ/ር አብይ እየወሰዱት ያለው እርዳታ የማፈላለግ እርምጃ የሚደነቅ ነው። ከቻይናዊው ቢሊየነር ጃክ ማ ጋር በመነጋገር ለአፍሪካ ያስገኙት የህክምና ቁሳቁስ የሚደነቅ ነው።

ዶ/ር አብይ በዲያስፖራው ተስፋ የቆረጡ ይመስለናል። በዚህ ሰዓት ዋናው አጋር ዲያስፖራው መሆን እንዳለበት እምነታችን ነው። የዲያስፖራው መልስ ቀዝቃዛ እንኳን ቢሆን፣ አገሩን እንዲረዳ ጥሪ ማድረጉ አይከፋምና ይሞክሩ እንላለን።

በአጠቃላይ ዶ/ር አብይ ባለፉት 3 ቀናት የወሰዱዋቸው እርምጃዎች፣ የዘገዩበትን ጊዜ የሚያካክስ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ለአንድ ጉዳይ ትኩረት ሲሰጡ ጥሩ አመራር መስጠት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።  ይህ ትኩረታቸው በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይበታተን አደራ እንላለን።

ኮሮና ቫይረስ የመሪዎችን ብቃት እየፈተነ ነው። ይህን ፈተና አሸንፎ ለመውጣት ሙሉ ጊዜንና ሃይልን በሽታውን በመከላከል  ላይ ማዋል ይገባል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: