ለግብጽ ዛቻ ቁብ ያልሰጠው መንግስት ግድቡን ከ3 ወራት በሁዋላ ውሃ መሙላት ይጀምራል

(ERF) ግብጽ ኢትዮጵያ ያለ ስምምነት ውሃ መሙላት እንዳትጀምር ወታደራዊ ማስፈራሪያዎችንና የዲፕሎማሲ ዘመቻዎችን ስታካሂድ ቆይታለች። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣኖቿ የአረብና የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በሮች ሲያንኳኩ ሰንብተዋል። በአረብ አገራት በኩል፣ ከሱዳን በስተቀር፣ “ከጎናችሁን ነን” የሚል ተሰፋ አግኝተዋል። ይሁን እንጅ የአረብ አገራቱ ትኩረት በኮሮና የተነሳ ተበታትኗል። በኢትዮጵያ በኩልም እንዲሁ በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ በቀድሞው ፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና በቀድሞው ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት የዲፕሎማሲ ዘመቻ ተካሂዷል። ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ሃይሏን ማሳየትና “ ትነኩኝና አሳያችሁዋለሁ” በማለት ለማስፈራሪያው ማስፈራሪያ መስጠት ጀምራለች።

የሁለቱ አገራት ውዝግብ እንደቀጠለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከ 3 ወር በሁዋላ ውሃ በመሙላት ወደ የካቲትና መጋቢት ወር አካባቢ 700 ሜጋ ዋት ሃይል ለማመንጨት ሙከራ እንደሚያደረግ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል።

ግድቡ በአሁኑ ሰዓት 72 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ስራው በተፋጠነ ሁኔታ እየሄደ እንደሆነም አስረድተዋል።

ግብጽ በአሜሪካው ዶናልድ ትራምፕ ላይ የነበራት ተሰፋ እየተሟጠጠ ነው። በአሁኑ ሰዓት የግብጽም ሆነ የአሜሪካ መንግስት ሙሉ ጊዚያቸውን ኮሮናን በመከላከል ላይ እያዋሉ ነው። ግብጽ 2 ታላላቅ ጄኔራሎችን በሞት አጥታለች። ሰራዊቷም ጸረ ተዋስያን መድሃኒቶችን በመርጨት ላይ ተሰማርቷል ። ኢትዮጵያ አሁን የሚታየውን የኮሮና ስርጭት በዚህ መጠን ጠብቃ የምትቆይ ከሆነ፣ የህዳሴውን ግድብ በተያዘለት ጊዜ የማጠናቀቅ ሰፊ እድል ይኖራታል። ይሁን እንጅ የውጭ ገበያው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ፣ የግድቡም ግንባታ በገንዘብ እጥረት የተነሳ ሊዘገይ ይችላል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም ተበራክተዋል።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: