በዚህ አያያዙ ኦነግ ሸኔ ጠ/ሚኒስትሩንም ከመግደል አይመለስም

ኦነግ ሸኔ የመንግስት ባለስልጣናትን እየነጠለ የመግደልና ሽብር የመንዛት ስትራቴጂ ይከተላል። ይህን ስትራቴጂውን ቀደም ብሎ በነቀምቴ ባለስልጣናት፣ በቅርቡ በለገጣፎ ፖሊስ አዛዥ፣ ዛሬ ደግሞ በነቅምቴ የቀድሞ የአስተዳደርና ደህንነት ሃላፊ አቶ ተሾም ገነቲ ላይ ተግባራዊ አድርጎታል። ኦነግ ሸኔ እስካሁን በያቅጣጫው ከ 50 ያላነሱ የመንግስት ባለስልጣን አንድ በአንድ እያለቀመ አጥፍቷቸዋል።

ይህንን ግድያ ለማስቀረት የኦሮምያ ክልል መንግስትና የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህ ጥረታቸውም አብዛኞቹን የሽኔ አባላት ትጥቅ ለማስፈታት ችለዋል። ትጥቅ አንፈታም ያሉትንም ቢሆን በሽምግልና ለማስገባት ተሞክሮ የተወሰነ ውጤት አግኝተዋል። ይሁን እንጅ ሁሉንም ሽኔዎች በሽምግልና ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለስ አልተቻለም። በተለይ በጃል መሮ የሚመራው ሃይል፣ ተዋግቶ መሞትን መርጧል።

ጠ/ሚ አብይ የመከላከያ ሰራዊቱን የሸኔን ታጣቂ እንዲያጠፋ ከላኩት ወራት ተቆጠረዋል ። ሰራዊቱ አብዛኞቹን የሸኔ ታጣቂዎች እየተከታተለ ቢገድላቸውም፣ ሙሉ በሙሉ ግን ሊያጠፈቸው አልቻለም። ለዚህም በመንግስት በኩል ሶስት ምክንያቶች ይቀርባሉ። አንደኛው ምክንያት አብዛኞቹ ታጣቂዎች ጥቅጥቅ ወዳሉ ጫካዎች በፍጥነት ስለሚሸሹ በቀላሉ አድኖ እርምጃ መውሰድ አልተቻለም። የጋምቤላ፣ ደቡብ፣ ኦሮምያና የቤንሻንጉል አካባቢ ጫካዎች ለሸማቂዎቹ ጥሩ መሸሸጊያ ፈጥሮላቸዋል። በሞያሌ በኩል ያሉት ደግሞ በኬንያና ኢትዮጵያ ድንበር እየተመላለሱ ጥቃት ይፈጽማሉ። የመከላከያ ሰራዊቱ ከተሞችንና አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎችን ከኦነግ ሸኔ እጅ ማስጣል ቢችልም፣ ጫካውን ግን ከእጃቸው ማስጣል አልቻለም።

ሁለተኛው ምክንያት፣ ህዝቡ በቀድሞና በአሁኖቹ ባለስልጣናት ቂም በመያዙ በተወሰነ መጠን የሸኔ ደጋፊ መሆኑ ለታጣቂዎቹ ረድቷቸዋል። በወለጋ አካባቢ የአብይ መንግስት በበጎ አይን አይታይም። የተወሰነው ክፍል የሸኔን አላማ ደግፎ ለሸኔ አባላት መረጃ፣ ምግብና ሌሎችንም አስፈላጊ ነገሮች ያቀርባል። አንዳንዱ ደግሞ የሸኔ ተዋጊዎችን ቤቱ ደብቆ በሌሊት ይሸኛል። የሸኔ አባላትም ቀን ቀን ከህዝቡ ጋር ሰላማዊ መስለው እየዋሉ፣ ማታ ማታ ስራቸውን ይሰራሉ። መከላከያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ፣ ግንኙነቶችን ለመበጠስ የሚያደርገው ጥረት የተወሰነ ውጤት ቢያስገኝለትም፣ ሙሉ በሙሉ ግን ችግሩን ለመቆጣጠር አላስቻለውም። ከዚህም ሌላ ሸኔን ይደግፋሉ የሚባሉ ነዋሪዎች በመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ የበቀል ጥቃት ስለተፈጸመባቸው ሳይወዱ በግድ የሸኔ ደጋፊዎች ሆነዋል። ሸኔን የማይደግፉትም ቢሆኑ፣ ለምን አልደገፋችሁም እየተባሉ በሸኔ ደጋፊዎች ማስፈራሪያ ስለሚደርስባቸው ያዩትን እንኳን ለመናገር አይደፍሩም። በዚህ የተነሳ ሽኔን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አልተቻለም።

በሶስተኛ ደረጃ ሸኔ ከመንግስት እና ከኦሮሞ ፖለቲከኞች እንዲሁም ከአንዳንድ ባለሃብቶች ድጋፍ የሚያገኝ መሆኑ፣ የመከላከያ ሰራዊቱን ስራ ፈተና የበዛበት እንዲሆን አድርጎታል። የአብይን መንግስት ከውስጥ ሆነው የሚገዘግዙ፣ በተለይ የአቶ ለማ መገርሳና የአቶ ጀዋር መሃመድ ደጋፊዎች፣ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ለኦነግ ሸኔ መረጃዎችን እያቀበሉ ታጣቂዎቹ በፍጥነት እንዲሸሹ ያደርጉዋቸዋል። በዚህ ላይ አብይን አምረርው የሚጠሉት የኦሮሞ ምሁራንና የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ አብይ ሆን ብሎ የሽምግልና ጥረቱን እያደናቀፈ እንደሆነ በመናገር ለሸኔ አባላት የሞራልና የፖለቲካ ድጋፍ ይሰጡዋቸዋል። ችግሩ ያለው መንግስት ላይ እንጅ ሸኔዎች ላይ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ቅስቀሳ በማድረግ እወነተኛው የችግሩ ምንጭ እንዳይታወቅና መፍትሄም እንዳይመጣ ያሴራሉ። አቶ ጃዋርን የመሳሰሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦነግ ሽኔ አባል ነን ለማለት ባይደፍሩም፣ በየጊዜው መንግስት በሸኔና በደጋፊዎቹ ላይ የሚወስደውን እርምጃ በማውገዝ እና አቤቱታዎችን በማቅረብ ፣ የኦሮሞ ህዝብ ከመንግስት ጎን ቆሞ ኦነግ ሸኔን እንዳይዋጋ ልቡን ይከፋፍሉታል።

በእነዚህ ሁኔታዎች የተበረታታው ኦነግ ሸኔ አንድ አንድ እያለ ግድያውን አጠናክሮ እየገፋበት ነው። የጦር መሳሪያ ችግር የለበትም። የገንዘብ ችግርም የለበትም። ከህወሃት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ባይኖረውም፣ በተወሰነ ደረጃ በእጃዙር እየተደገፈ እንደሆነ ይነገራል። ይህም ሌላ ጉልበት ሰጥቶታል።

ኦነግ ሸኔ በምዕራብ የአገሪቱ አካባቢ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑ አያጠያይቅም። የኦሮምያ ክልል በርካታ የልዩ ሃይል አባላትን እያሰለጠነ ችግሩን በሃይል ለመፍታት እየሞከረ ነው። ይሳካ አይሳካ ለወደፊቱ የሚታይ ነው። አሁን ባለው ስውር አደረጃጀቱ ግን ኦነግ ሸኔ በጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ሳይቀር ግድያ ለመፈጸም ወደ ሁዋላ ከማለት አይመለስም። ጠ/ሚኒስትሩን  ለመግደል አቅም አይኖረውም ቢባል እንኳ በአቶ ሽመልስ አብዲሳና አቶ ታዬ ደንደአን በመሳሰሉት የኦሮምያ የበልጽግና ፓርቲ አባላት ላይ ጥቃት ከመሞከር አይመለስም። ኦነግ ሽኔ ቢዳከምም አልጠፋም። አጥፍቶ መጥፋት የሚለው ስትራቴጂም ሩቅ ባይሰደውም ጊዜያዊ ውጤት እያመጣለት ነው።

ሰይፈዲን

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: