በፋኖና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ያለው ፍጥጫ ቀጥሏል

የተሰጠው የጊዜ ገደብ በፍጥነት እየቀረበ ነው፤ አርበኛ መሳፍንት እጁን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም

(ERF) በፋኖና የአማራ ልዩ ሃይልን በካተተው የመከላከያ ሰራዊት መካከል ያለው ፍጥጫ እያየለ ሄዷል። የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ልዩነቱን በሽምግልና ለመፍታት ቢሞክሩም እስካሁን አልተሳካላቸውም። የጎንደር ከተማ የጸጥታው ምክር ቤት በፋኖ ስም ዝርፊያና ግድያ ይፈጽማሉ ያላቸው ታጣቂዎች፣ እስከ መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓም ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል። አርበኛ መሳፍንት ተሰፉና አርበኛ አረጋ ግን ” እጅ መስጠት የማይታሰብ” ነው ይላሉ። ሁለቱም ፋኖዎች “የህልውና ስጋት ስለተደቀነብን ተዋግተን እንሞታለን” እያሉ ነው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ  በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጸጥታ ከማስከበር ይልቅ ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሆነዋል በሚል ምክንያት የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርብ መቆየቱን ይናገራል።  ኢ መደበኛ አደረጃጀት ቀርቶ ፋኖዎች ወደ ፖሊስ ወይም ልዩ ሃይል እንዲጠቃለሉ፣ በእድሜ የገፉት ፋኖዎች ደግሞ መቋቋሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ እንዲመለሱ ሙከራ ማደረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ፋኖ አረጋ በበኩሉ ችግሩ የመንግስት ነው ይላል። ” እኛ ከመንግስት ጋር አብረን ለመስራት ፍላጎቱ ነበረን፤ መንግስት ግን በጠላትነት እያየ ሊያቀርበን አልፈለግም” ይላል አርበኛ አረጋ።

አርበና አረጋ አክሎም “መንግስት የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጠን፣ በጋራ ሆነን ጸጥታ እንድናስከበር እንዲሁም ወደ ልማት መዞር ለሚፈልገው የመቋቋሚያ ገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ብንጠይቅም፣ የመንግስት ባለስልጣናት እኛን እንደጠላት ከማየት ውጭ ሊተባበሩን ፈቃደኞች አይደሉም” ብሏል።

የአማራ ምሁራን ጉባኤ ባወጣው መግለጫ መንግስት ስርዓት ለማስከበር የሚወስደው እርምጃ ተገቢ ነው ብሏል፤ ይሁን እንጅ ፋኖዎች ወደ መንግስት የጸጥታ ሃይል የሚካተቱበት እንዲሁም መቋቋሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታም ይመቻችላቸው ሲል ጠይቋል።

ፋኖዎች ድርጅቶቻቸው እንዲፈርሱ ወይም በመንግስት ስር እንዲጠቃለሉ ፍላጎት የላቸውም። እነሱም ጦራቸውን እንደያዙ ከመንግስት ጋር እየተባበሩ ሰላም የማስከበር ስራ መስራትን ብቻ ይፈልጋሉ። መንግስት ግን በአንድ አገር መሳሪያ ታጥቆ ሰላም የማስከበር ብቸኛ ህጋዊ መብት የመንግስት እንጅ የአንድ ቡድን ሊሆን አይችልም የሚል ጠንካራ አቁም ይዟል። በነገራችን ላይ ፋኖ አንድ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መሪዎች የሚመሩ ብዙ ፋኖዎችና ቅርንጫፎች አሉ።

ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ የክልሉ የጸጥታ ሃላፊ በነበሩበት ወቅት፣ ፋኖ በመንግስት ሳይጠቃለል እራሱን ችሎ እንዲደራጅ እና ከመንግስት ጋር እየተባበረ ጸጥታ እንዲያስከብር ፍላጎት ነበራቸው። እንዲያውም አሳምነው የክልሉን ልዩ ሃይል በፋኖ ለመተካትና ብአዴንን ለማፍረስ ፍላጎት አለው በሚል የብአዴን ባለስልጣናት ውስጥ ለውስጥ ያስወሩበት ነበር። የክልሉ መንግስት አሳምነው ፋኖን እንዲያፈርሱ ትዕዛዝ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም አሳምነው ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ብ/ጄ አሳምነው በእነ ፋኖ አረጋ የሚመራውን የፋኖ ታጣቂ ሃይል ያለ ክልሉ መንግስት እውቅናና ፈቃድ ወደ ከሚሴና ሰሜን ሸዋ ( አጣዬ) ማሰማራታቸው በብአዴንና በአሳምነው መካከል ያለው ልዩነት ወደ ማይታረቅበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል። የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ልዩ ሃይሉ ጥቃቱን መመከት ይችል ነበር የሚል አቋም ነበራቸው። ወደ ከምሴና ሰሜን ሸዋ የዘመተው ፋኖ የተጠበቀውን ያክል ውጤት ባለማምጣቱ እንዲሁም በአካባቢው ህዝብ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጉዳት አድርሷል በመባሉ፣ የክልሉ መንግስት የብ/ጄ አሳምነውን ስትራቴጂና የአመራር ብቃት ጥያቄ ውስጥ እያሰገባና አሳምነው ስልጣን መልቀቅ እንዳለባቸው እያመነ መጣ። በዚህ መሃል በፋኖ አረጋና በአሳምነው ጽጌ መካከል በውጊያ ስትራቴጂና አመራር ዙሪያ ልዩነት ተፈጠረ። ፋኖ አረጋም “የአሳምነውን ትዕዛዝ አልቀበልም፣ አልዋጋም ብሎ” ተዋጊዎቹን ይዞ ተመልሷል። አሳምነው በዚህ ሃይል ላይ ቂም ይዞ ቆይቷል። እርምጃ እንዲወሰድበትም ፍላጎት ነበረው። የአረጋ ሃይል በተወሰነ መጠን ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ሲነገር ቢቆይም፣ የሰሞኑ ሁኔታ ግን ልዩነት እየሰፋ እንደመጣ የሚያሳይ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት የመከላከያ እና የልዩ ሃይል አባላት ጎንደር ላይ ካምቱን ሰርቶ በተቀመጠው የፋኖ ሃይል ላይ ድንገተኛ ከበባ በማድረግ ትጥቅ ለማስፈታት ተንቀሳቅሰው ነበር። የፋኖ አባላቱ በመከላከያና በልዩ ሃይል አባላት ላይ ተኩስ ከፍተው የተወሰኑትን ገድለውና አቁስለው በእነሱ ላይ ጉዳት ሳይደርስባቸው ከበባውን ሰብረው ወጥተዋል። ይህን ተከትሎም በዳባት እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ፋኖዎችን ለመያዝ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ቦታው አቅንቶ፣ ፋኖዎች እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ለማድረግ እየሞከረ ነው።

በዳባት የአርበኛ መሳፍንት ሃይል ከሰራዊቱ ጋር ውጊያ የገጠመ ቢሆንም፣ በአገር ሽማግሌዎችና በቀሳውስት ጥረት እንዲቆም ተደርጓል። አርበኛ መሳፍንት ግን እጁን ለመንግስት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም።

የጎንደር ከተማ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ያበቃል። አርበኛ አረጋ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የሚመለሱለት ከሆነ ምናልባትም ከመንግስት ጋር ተደራድሮ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ሊያደርግ ይችላል። መንግስት ጥያቄውን የማይፈታና በሃይል ለመፍታት እሞከራለሁ ካለ ራሱንና ድርጅቱን ለመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል። በአረጋ ስር ምን ያክል ታጣቂ ፋኖዎች እንዳሉ አይታወቅም።

ፋኖ መሳፍንት ከፋኖ አረጋ ጋር ሲተያይ ጠንከር ያለ አቋም አለው። ፋኖ በአደረጃጀቱ መቀጠል አለበት ብሎ ያምናል። በተለይ “ትግራይ አፈሙዟን በእኛ ላይ ደግና እያለ፣ እኛ ድርጅታችንን ለማፍረስ መጠየቅ የለብንም” የሚል ጠንካራ አቋም አለው። በርካታ ተዋጊ ፋኖዎች የሚገኙት በአርበኛ መሳፍንት ስር በመሆኑ፣ ከእርሱ ጋር የሚደረገው ውጊያ ደም አፋሳሽ ይሆናል። የዳባትና የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጠው በመሆኑ፣ ግጭት ቢነሳ በቀላሉ ላይበርድ እንደሚችል የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።

ፍጥጫው አይሏል። የተሰጠው የጊዜ ገደብም በፍጥነት እየበረረ ነው። እስካሁን ይህ ነው የሚል ተስፋ አልተገኘም። መጨረሻው ምን ይሆን? እየተከታተል እናቀርባለን።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: