እስክንድር ነጋና ፋኖ

የእስክንድር ፖለቲካ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለፕሬስ ነጻነት በከፈለው ዋጋ ከአገር አልፎ አለማቀፍ እውቅና አስገኝቶለታል። በጽናቱና አይበገሬነቱ የብዙዎችን አድናቆት ማትረፉ የሚያከራክር አይደለም። ይሁን እንጅ የፕሬስ መብት ተሟጋችነቱን ትቶ ወደ ፖለቲካው አለም መግባቱን ካሳወቀ በሁዋላ፣ እስክንድር አወዛጋቢ ከሆኑ የኢትዮጵያ ፖለተከኞች ተርታ ተሰልፏል ። ለኢትዮጵያ ነጻነትና ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚለው እስክንድር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የብሄር ፖለቲካው እየጣፈጠው ሲሄድ እያየን ነው። ከብሄርተኞች ጋር የጀመረው ወይም ያደሰው ፍቅር፣ የቀድሞ የትግል ጓደኞቹ ሳይቀር ” ይህን ሰውዬ ምን ነካው?” እንዲሉ አድርጓቸዋል።

“የእስክንድርን ፍላጎትና አካሄድ እንኳን እኛ ራሱም አያውቀውም” ይላል አንድ ለረጅም ጊዜ በትግል አብሮት ያሳለፈው ጓደኛው። “እስክንድርን የምትጨብጠው ሰው ሊሆን አልቻለም፤ ምንድነው የምትፈልገው ብለህ ስትጠይቀው አንተን የሚያስደስትህን ነገር ብቻ ነግሮህ ይሸኝሃል እንጅ እውነተኛ ፍላጎቱን ማወቅ አይቻልም፤ ድብቅ ሰው ነው ” ይላል ሌላው።

እስክንድር ከቀድሞ የትግል አጋሮቹ እየራቀ፣ ከአማራ ብሄርተኞች ጋር ደግሞ እየተጣበቀ ነው። በቅርቡ ከመኢአዱ አቶ ማሙሸት አማረ ጋር ቅንጅት ለመፍጠር መስኗል። ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን) ጋር መጣመር ቢፈልግም፣ የአቶ ልደቱ አያሌው ኢዴፓ በጥምረቱ ይግባ የሚለው የአብን አቋም ስላላስደሰተው ” አልቀላቀልም” ብሏል። ልደቱ ካልገባ ግን እስክንድር ከአብን ጋር ጥምረት ለመመስረት ችግር የለበትም። እንዲያውም አቶ ማሙሸት አማረ፣ አብንን በማቋቋም እኔና እስክንድር ከፍተኛ ሚና ተጫውተናል ብሎ በአደባባይ መስክሯል።

እስክንድር የአብይን መንግስት ብቻ ሳይሆን፣ ኢዜማንም አጥብቆ ይቃወማል። ኢዜማ “በአዲስ አበባም በአማራ ክልልም አንድ ድምጽ ማግኘት የለበትም” ይላል። አብረውት ከታገሉ የኢዜማ ጓደኞቹም ጋር ተራርቋል። የአብይ ተለጣፊዎች ናቸው ይላቸዋል። በእስክንድር እምነት እነሱም መጥፋት አለባቸው።

This image has an empty alt attribute; its file name is image-22.png

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በባህርዳር ከተማ የጄ/ል አሳምነው ታጣቂ ቡድን በባለስልጣናት ላይ ግድያ ሲፈጽም እስክንድር ባህርዳር ነበር። የእስክንድር አጋር የነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና የእስክንድር ዋና ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው አቶ ስንታየሁ ቸኮል በዚሁ ሰበብ ታስረው ተለቀዋል። እስክንድር ያለው አለማቀፋዊ ዝና ከእስር እንደታደገው ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ግን እስክንድር ባህርዳር ስለተገኘ ብቻ በድርጊቱ እጁ ነበረበት ማለት አይቻልም። ይሁን እንጅ ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎች እስክንድርን ማኖ ለማስነካት አስበው እንደነበር አያጠራጥርም። የእስክንድር የፖለቲካ ብስለት ጉድለትም የሚታየው እዚህ ላይ ነው።

እስክንድር ከአብን፣ አብንም ከጄ/ል አሳምነው ጋር የነበራቸው ግንኙነት የቀጥታ ሳይሆን ኦነግንና ህወሃትን ኢላማ ያደረገ እንደነበር ይታወቃል። ለእስክንድርም ሆነ ለብዙ የአማራ ብሄርተኞች አብይ አህመድና ታከለ ኡማ፣ ታከለና ጀዋር ሙሃመድ አንድ አላማ ያላቸው አንድም ሶስትም ናቸው።

እስክንድር ባልደራስን ሲያቋቁም ሁለት አላማዎች ነበሩት። አንደኛው ከንቲባ ታከለ ኡማን የኦነግ ወኪል አድርጎ በመፈረጅ ከስልጣን የሚወገድበትን መንገድ መሻት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ጀዋር መሃመድ “አዲስ አበባ የኦሮምያ ናት” የሚለውን ቅዠቱን ማክሸፍ ነበር። ሁለቱም አላማዎች ለስክንድር ከውጭም ከውስጥም ብዙ ደጋፊዎችን አስገኝተውለታል። ከዲያስፖራውም ብዙ ገንዘብ እንዲሰበሰብ እረድቶታል። ነገር ግን ታከለ ኡማ እንደሚወራው የኦነግ ስራ አስፈጻሚ አለመሆኑ ሲታወቅ ወይም ጃዋርና አብይ ለሞት የሚፈላለጉ ጸበኞች እንደሆኑ እየታወቀ ሲመጣ እንዲሁም ዶ/ር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ለህዝቧ ብልጽግና የሚታገል እንጅ እንደሚባለው ኦሮምያን የመገንጠልም ሆነ አዲስ አበባን የኦሮሞ ብቻ የማድረግ ፍላጎት እንደሌለው ሲታወቅ፣ የእስክንድር ፖለቲካ እንደ ጃዋር ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ገብቷል። እስክንድር የአዲስ አበባን ህዝብ በበቂ ሁኔታ አሳምኖ በታከለ ወይም በአብይ ላይ እንዲነሳ የማድረጊያ ነዳጁን ጨርሷል።

እስክንድር ወደ ፖለቲካ ለመግባት ፍላጎት እንዳልነበረውና በእነ ጃዋርና ታከለ ኡማ ተገፋፍቶ እንደገባ ይናገራል። እውነታው ግን ሌላ ነው። እስክንድር አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግፊት ወደ ፖለቲካ እንደገባ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ይህ ደግሞ እስክንድር አንድን ውሳኔ የሚወስነው በስሜትና የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት ለማሟላት ብሎ እንደሆነ የሚያሳይ፤ በፖለቲካ ግንዛቤውም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

እስክንድር በአዲስ አበባ ባልደራስን ወክሎ በምርጫ እንደሚወዳደር አስታውቋል። ብልጽግና አዲስ አበባ ላይ ምንም ድምጽ እንደማያገኝ፤ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን የእስክንድርን ቡራኬ ያላገኘው ኢዜማም አንድም ወንበር እንደማያገኝ በአደባባይ ምሏል። “ብልጽግና ካሸነፈ እኔም ጓደኞቼም ስልጣናችንን እናስረክባለን” ሲል ተናግሮ አስጨብጭቧል። ከአሜሪካ ዲያስፖራ የተሰጠውን ቃል አክብሮ እንደሚያስፈጽምም ቃለ መሃላ ፈጽሟል። ይህን በሰላም ማከናወን የሚችል ከሆነ እሰየው ነው። ህዝብ በመረጠው ሰው ሊተዳደር ግድ ነውና። ችግሩ የሚመጣው ይህን ቃል ለመፈጸም ሲባል ከሰላማዊ መንገድ ማፈንገጥ ከተጀመረ ነው።

እስክንድር የሃይልን አማራጭ ከሚያስቡ ሃይሎች ጋር እየተቀራረበ መምጣቱ፣ ለአድናቂዎቹና ደጋፊዎቹ ጭንቀትን እየፈጠረ፣ እሱን ለመምታት ለሚያስቡት ሃይሎች ደግሞ ጥሩ ድንጋይ እያቀበለ ነው። በቅርቡ ወደ ጎንደር በማምራት ከፋኖ መሪዎች ጋር ተነስቶ የለጠፈው ፎቶ የመንግስት ባለስልጣናት የእስክንድርን አካሄድ በጥርጣሬ እንዲመለከቱት በር ከፎቶላቸዋል። ልብ በሉ ከዚህ ቀደም ከብ/ጄ አሳምነው ጽጌ ጋር በተያያዘ ስሙ ይነሳ ነበር። አሁን ደግሞ ከፋኖ ጋር። እስክንድር ከፋኖ ጋር ተያይዞ የሚነሳበትን ትችት እስካሁን በበቂ ሁኔታ አላስተባበለም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ለፋኖ ድጋፉን ለመስጠት ሲል ኢትዮጲስ የተባለውን መጽሄቱን ከሞት አስነስቷታል። በኢትዮጲስ ስም ለፋኖ ያለውን ድጋፍ ሰፊ የዜና ሽፋን በመስጠት አጋርነቱን ገልጿል።

ፋኖ አወዛጋቢ የሆነ ሃይል ነው፤ ህወሃትን ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋትነት የከፈለ ቢሆንም፣ በከፊል በመንግስት ችግር፣ በከፊል በራሳቸው በፋኖዎች ችግር ለአማራ ክልልና ህዝብ አስቸጋሪ እየሆኑ መጥተዋል። መንግስት ይህን ሃይሎ በአንድ እዝ ስር ለማስገባት ወይም ትጥቅ እንዲፈታ ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ  የአማራ ምሁራን ደግፈውታል። እስክንድር ግን ፋኖን መደገፍን መርጧል። ይህም በመንግስት ሃይሎች ለጥቃት እንደሚያጋልጠው አያጠያይቅም። ፋኖ የፖለቲካ ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምድ ወይም ከክልሉ ጋር በአንድ እዝ ስር ሆኖ እንዲያስፈጽም እንደመምከር፣ የፋኖ ደጋፊ ሆኖ መቅረብ በፋኖ ለሚሰቃየው የአማራ ህዝብ አለማሰብ ነው።

የፋኖ ሊ/መንበር የተባለው ሰለሞን አጣናው ፋኖ የወልቃት፣የራያ፣የደራ እና የመተከል የአማራ ወሰኖች ወደነበሩበት ሳይመለሱ ፋኖ ትግሉን እንደማያቆም መናገራቸውን ለኢትዮጲስ ተናግሯል። ይህን መጠየቅ መብት ነው። ችግሩ ግን ፋኖ እነዚህን አካባቢዎች በሃይል የማስመለስ ፍላጎት ያለው መሆኑ ነው። እክንድርም ፋኖን ሲደግፍ እነዚህ ጥያቄዎች በሃይል እንዲመለሱ ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው። ለመሆኑ በአሁኗ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን በሃይል እናስፈጽም ቢባል ትርፉ መተላለቅ አይደለምን? በየክልሉ መሳሪያ የታጠቀው ፋኖ ብቻ ነውን?  እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን በውይይትና በሰላም መፍታት አይሻልምን? ያስ ቢሆን በአማራ ክልል ስር ሆኖ መደራጀት አይሻልምን? በአንድ ክልል ሁለት እና ሶስት እርስ በርስ ለግድያ የሚፈላለጉ የጦር ቡድኖችን ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ? ለመሆኑ የአማራ ባለሃብትና ህዝብ ለማን ነው የሚገብረው? ለታጣቂዎች ወይስ ለክልሉ መንግስት? ፋኖዎችም እኮ በፊናቸው አስገድደው ገንዘብ ይቀበላሉ። የፋኖ በዚህ ሁኔታ መቆየት ከማንም በላይ የሚጎዳው የአማራን ህዝብ ነው። አንድነቱ እንዲከፋፈል፣ ለአማራ ክልል መንግስትና ለፋኖ መንግስት እንዲያድር፣ ለሁለት መንግስት እንዲገብር የሚያደርገው ነው። በሂደቱም ሁለቱ መንግስቶች ሲጣሉ፣ የክልሉን ህዝብ ከሁለት ተከፍሎ እርስ በርሱ እንዲያዋጋ ያደርገዋል።

ማንኛውም የሃይል አማራጭ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመነ መሳፍንትን የሚጋብዝ መሆኑን ለስክንድርና ለመሰሎቹ ማስረዳት ተገቢ ነው።

እስክንድር እየተከተለው ያለው የፖለቲካ መንገድ አንድ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ የሚወስደው ነው። የሚሄድበትን መንገድ እንኳንስ ሌሎች ራሱም በግልጽ የተረዳው አይመስለኝም።

ሶፎኒያስ አበበ

ጎንደር  

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: