የቡድን 20 አገሮች ለደሃ አገሮች ድጋፍ ለማድረግ ተስማሙ

(ERF) በአለማችን በኢኮኖሚ አቅማቸው የዳበሩ የቡድን 20 አገራት ዛሬ በሳውድ አረቢያው ንጉስ ሰልማን አማካኝነት የቪዲዮ ኮንፍረስ አድርገዋል። የኮንፈረንሱ ዋና አላማ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ በአለም ላይ የተፈጠረውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ መናጋት ለማስተካከል ነው። አገሮቹ ወደ 5 ትሪሊየን የሚጠጋ ገንዘብ ኢንቨስት ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ኮሮናን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ፣ የመድሃኒትና ሌሎችንም የአቅርቦት ችግሮች ለመከላከልም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በሽታውን ለመከላከል የሚያስችለውን መድሃኒት ለማዘጋጀት የመረጃ ለውጥጥ እንዲደረግም ተስማምተናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ባልታዬ ሁኔታ ሁሉም አገራት ያለምንም ውዝግብ ስብሰባውን አካሂደዋል። ፕ/ት ትራምፕ በሽታውን ለመቋቋም የጋራ ጥረት ያስፈልጋል በማለት ከሌሎች አገራት ጋር ለመተባበር ቃል ገብተዋል።

ሃብታም አገሮቹ ለደሃ አገሮች ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ተሰማምተዋል። የአለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ( IMF) እና የአለም ባንክ ለደሃ አገራት ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት የአለም የገንዘብ ድርጅት መጀመሪያ ላይ አቅርቦት የነበረውን የ50 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ፍላጎቱን አሳይቷል። በአለም ባንክ በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም። ይሁን እንጅ ደሃ አገራት ለእዳ የሚከፍሉትን ገንዘብ በሽታውን ለመቆጣጠር እንዲያውሉት ሁለቱ ባንኮች አበዳሪ መንግስታቱን ጠይቀዋል። በዛሬው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ የታየው መንፈስ ጥሪያቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያመላክት ነው።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ አፍሪካን በመወከል የ 150 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለቡድን 20 አገራት አቅርበዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ይህን ሃሳባቸውን በታዋቂው የፋይናንሻል ታይምስ ላይ በማስፈር ለአለም መንግስታት እንዲደርስም አድርገዋል። ኢትዮጵያ የቡድን 20 አገራትን ስብሰባ አትሳተፍም ይሁን እንጅ የዚሁ ቡድን አባል የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በመሪዋ ስሪል ራማፎሳ አማካኝነት የአፍሪካን ጥያቄ አቅርባለች።

ኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ካጋጠማቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። ታዋቂው አየር መንገድ ከ30 በላይ ወደ ሚጠጉ አገራት መብረር አቋሟል። በዚህም እስካሁን አገሪቱ ከ 190 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ አጋጥሟታል። የአበባ ኩባንያዎች ስራ በማቆማቸውም እንዲሁ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ቀንሷል። ብዙ ሰራተኞችም እየተቀነሱ ነው። ይህን ለመቋቋምና በኮሮና ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚ መልሶ ለማንሳት የአለም አገራት ድጋፍ እጅግ ወሳኝ ነው።

የዛሬው የቡድን 20 አገራት ስብሰባ በመግለጫው ላይ ያሰፈረውን ቃል ወደ ተግባር የሚለውጠው ከሆነ፣ የኢኮኖሚ ቀውሱን በሂደት መቋቋም ይቻላል። ለማንኛውም ግን ሁለቱ የአለም ታላላቅ አበዳሪ ባንኮች ( አይ ኤም ኤፍና የአለም ባንክ) የሚሉትን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንሰማለን።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: