የሃይማኖት ተቋማትን ባንኮችንና ሃኪሞችን በተመለከተ ተጨማሪ ትዕዛዝ ተሰጠ

(ERF) መንግስት  የኮርና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ዛሬ ባወጡት ተጨማሪ መመሪያ ላይ አብያተ ክርስቲያናትና መስኪዶች ሊዘጉ የሚችሉበትን ፍንጭ ሰጥቷል።

የፌዴራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት አለው የሚለው መመሪያው፣ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገጉት እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት ዜጎች አካላዊ ርቀት የመጠበቅን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አዟል። ፌደራል ፖሊስም ህዝቡ አስፈላጊውን እርቀት መጠበቁን እንዲከታተል ታዟል።

የዛሬው መመሪያ የሃይማኖት ተቋማት ላልተወሰነ ጊዜ ሊዘጉ የሚችሉበትን ፍንጭ የሚሰጥ ነው። መንግስት እስካሁን በድፍረት የሃይማኖት ተቋማት እንዲዘጉ ትዕዛዝ አልሰጠም። የሃይማኖት ተቋማቱም አገልግሎት ለማቋረጥ እስካሁን ፈቃደኞች አልሆኑም። ሳውድ አረቢያና ቫቲካንን ጨምሮ በርካታ አገሮች የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል።

በሌላ በኩል ብሄራዊ ባንክ በሞባይል የሚደረገውን የገንዘብ ክፍያና ዝውውር ጣሪያ ከፍ እንዲያደርግ ታዟል

እርምጃው ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው በተጨማሪ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን አላስፈላጊ ንክኪ በማስቀረት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።

ከፍተኛ ችግር ያጋጠመውን የአበባ ገበያ ለመታደግም ብሄራዊ ባንክ በአበባ የመሸጫ ዋጋ ላይ የጣለውን ዝቅተኛ ተመን እንዲያነሳ ታዟል።

በሽታውን ለመከላከል ከውጭ እቃዎችን የሚያስመጡ ዜጎች ቅድሚያ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጣቸው፣ እንዲሁም በተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ዙሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ አማራጮችን እንዲያፈላልግ እንዲሁም ብሄራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊዮን ብር ለብድር ዝግጁ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተላልፏል።

እንዲሁም  የሃኪሞችን ችግር ለመቅረፍ፣ ጡረታ የወጡና በትምህርት ላይ የሚገኙ ሀኪሞች ለብሄራዊ ግዳጅ ዝግጁ እንዲሆኑ ታዘዋል።

እስካሁን 16 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ታውቋል። ከተያዙት መካከል ሁለቱ የ 24 እና 28 አመት ወጣቶች ናቸው።

Comments are closed.

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: