ኢትዮጵያ ውዝግብ የሚያስነሳ የውሃ ሙሌት አማራጭ ይፋ አደረገች

(ERF) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገጻቸው ይፋ ያደረጉትን የውሃ አሞላል ሰነድ በመዳሰስ ሪፖረተር ዘገባ ያቀረበ ሲሆን፣ ሰነዱ ብዙ አወዛጋቢ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ይዟል።

በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው አማራጭ የግድቡን የውሃ ሙሌት ሂደት በሁለት ምዕራፍ የሚከፍል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ከ 2 እስከ 5 አመታትን እንደሚወስድ ይገልጻል። በዚህ አመት 4 ቢሊዮን 900 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመያዝ መታቀዱን በሚቀጥለው የ2013 የክረምት ወቅት ደግሞ 13 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመሙላት መታቀዱ ተገልጿል።

በሁለት አመታት 18 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን  ሜትር ኪዩብ ውሃ ከተሞላ በሁዋላ፣ 2 ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ።

ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌትም ግድቡ 49 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እስከሚይዝ ድረስ ከ 2 እስከ 5 አመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም መታቀዱ ተመልክቷል።

አጠቃላይ ግድቡ 74 ቢሊዮን ሜኩ ውሃ የሚይዝ ቢሆንም፣ የመጀመሪያው ዙር ማለትም 49 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ከተሞላ በሁዋላ ቀሪው 25 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው ውሃ በማንኛውም የዝናብ ወቅት እየተሞላ እንደሚሄድ ተመልክቷል።

ሚኒስቴሩ ድርቅና አስከፊ ድርቅ የሚሉትን አሻሚ ቃሎች መልስ ለመስጠት በሁለት አመታት ውስጥ የመጀመሪያው 18 ቢሊዮን ሜኩ ውሃ ከተያዘ በሁዋላ ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ ከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ወደ ቀጣዩ ክረምት እንደሚተላለፍ፣ በሁሉም የሙሌት ምዕራፎች ውሃው ከ 35 ቢሊዮን ሜኩ በታች ከሆነ ደግሞ ውሃ ሳይጠራቀም፣ ሃይል ብቻ አመንጭቶ እንዲያልፍ ይደረጋል ብሏል።

ኢትዮጵያ ይህን አማራጭ ያቀረበችው ግብጽና ሱዳንን ላለመጉዳት በማሰብ መሆኑን ትገልጻለች። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር ማለትም 49 ቢሊዮን ሜኩ ውሃውን በ3 አመት መሙላት ስትችል ለ 5 አመታት ማራዘሟ ለታችኛው አገራት በማሰብ መሆኑንም ሰነዱ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ያቀረበችው አማራጭ ፍትሃዊ ቢመስልም፣ አገሪቱን እንዳይጎዳትና ለውዝግብም በር እንዳይከፍት ተፈርቷል። በሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሂደት ላይ ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ ከ 31 ቢሊዮን ሜኩ በታች ቢሆን፣ እንዲሁም ተደጋጋሚ ድርቅ ተከስቶ ውሃው በየክረምቱ ከ 31 ቢሊዮን ሜኩ በታች ቢሆን፣ ግድቡ ውሃ ሳይዝ ለረጅም አመታት ሊቀጥል እንደሚችል ይህም ኢትዮጵያን እንደሚጎዳና ለውዝግብ በር እንደሚከፍት ያሳያል።

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ሰነድ ድርቅ አይከሰተም በሚል እምነት እንደሆነ ከሰነዱ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጅ የአለም የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭ በሚሆንበት በዚህ ወቅት፣ ተከታታይ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አስቦ ሌሎች አማራጭ እቅዶችን ማዘጋጀት እንደሚገባ የሚመክሩ አሉ።

ግብጽ ይህን አማራጭ ትቀበለው አትቀበለው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: