ኮሮናን በባህላዊ መድሃኒት

ሰሞኑን ለኮሮና በሽታ አገር በቀል በሆኑ ወይም በተለምዶ ባህላዊ መድሃኒቶችን ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መገለጹን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። አንዳንዱ “አበጃችሁ’ ሲል ሌላው “አታሹፉ” ብሏል። ምንም እንኳን ዘመናዊው መድሃኒት ከባህላዊ መድሃኒቶች ተነስቶ ያደገ ቢሆንም፣ በዘመናዊ ትምህርት ያደጉ የኢትዮጵያ ልጆች ባህላዊ መድሃኒቶችን ለመጠቀም አይደፍሩም ብቻ ሳይሆን፣ መድሃኒቱን የሚቀምሙትን ሰዎች እንደ ኋላ ቀር በመቁጠር ይሳለቁባቸዋል። በዚህም የተነሳ ባህላዊ መድሃኒቶች በሚፈለገው መጠን አላደጉም። በዘመናዊ ትምህርት ሰልጥነው የመንግስት ስልጣን የሚይዙት መሪዎችም ባህላዊ መድሃኒቶች እንዲጎለብቱ እገዛ አያደርጉም።

የባህላዊ መድሃኒቶችን በተመለከተ የአለም የጤና ድርጅት (WHO) ምን ይላል?

የአለም የጤና ድርጅት ባህላዊ መድሃኒቶች እንዲጎለብቱ ለማድረግ እስከ 2023 የሚቆይ ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ባህላዊ መድሃኒቶች እጅግ ተፈላጊ መሆናቸውንና ተፈላጊነታቸውም እየጨመረ መሄዱን በስትራቴጂክ እቅዱ ላይ ጽፈዋል። የአለም የመድሃኒት ዋጋ እየጨመረ በመሄዱ እንዲሁም መድሃኒት እንደልብ ለማይገኝላቸው አንዳንድ በሽታዎች ባህላዊ መድሃኒቶች ተመራጭ የህክምና ዘዴ እንደሆኑም ዶ/ር ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

በአለም ላይ 179 አገሮች ባህላዊ መድሃኒቶችን ይጠቀማሉ። ካናዳ ከ 54 ሺ በላይ ባህላዊ መድሃኒቶችን መዝግባ ጥቅም ላይ ታውላለች።  በአፍሪካ ውስጥ 7 አገሮች ማለትም ቡርኪና ፋሶ፣ካሜሩን፣ ኮንጎ፣ ጋና፣ ማዳጋስካር፣ ማሊና ኒጀር የባህል መድሃኒቶችን ከዘመናዊው ጋር አጣምረው ይጠቀማሉ። በአውሮፓ ደግሞ አርሜኒያ፣ ካዛኪስታን፣ ሞልዶቫ፣ ሩስያ ፣ ታጃክስታን፣ ዩክሬን እና ኡዝቤክስታን በተመሳሳይ መንገድ ይጠቀማሉ። ቻይናና ቪቴናምም እንዲሁ የባህል መድሃኒቶች ዋና ተጠቃሚ ናቸው።  

ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የባህል መድሃኒቶችን እንደሚጠቀም የጤና ድርጅቱ መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ በባህላዊ መድሃኒቶችና እጽዋት ዙሪያ መጠነኛ ህግ ቢኖርም በበቂ ሁኔታ የተደራጀ እንዳይደለም የአለም የጤና ድርጅት ይገልጻል።

ከጤና ድርጅቱ በተገኘው መረጃ መሰረት ከ7 አመታት በፊት በኢትዮጵያ ከ 600 በላይ የባህል መድሃኒት ሰጪዎች ነበሩ ። አሁን ላይ ቁጥሩ ይጨምር ወይም ይቀንስ የታወቀ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ለኮሮና በሽታ መድሃኒት መፈለጋቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባ ነበር። በእርግጥ መድሃኒቱ የመጨረሻ ሙከራ ሳይደረግበት ለአደባባይ ማብቃት ህዝቡ ጥንቃቄ እንዳያደርግ ሊያዘናጋው ስለሚችል ተገቢ አልነበረም። ይሁን እንጅ ለኮሮና በሽታ መድሃኒት መፈለግ ያለበት በዘመናዊ ወይም በሳይንሳዊ ዘዴ ብቻ እንደሆነ ለማሳየትና ባህላዊውን ዘዴ ለማጣጣል የተሄደበት ርቀት ተገቢ አይደለም። ስለመድሃኒት እውቀቱ የሌላቸው ሰዎች፣ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ የሚመጣን እውቀት ማጣጣላቸው አላዋቂነታቸውን የሚያሳይ ካልሆነ ሌላ ሊባል አይችልም። የአለም የጤና ድርጅት ባህላዊ መድሃኒቶችን ለማሳደግ እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ፣ የኢትዮጵያ ምሁራን “ ባህላዊውን እውቀት” ማጣጣላቸው፣ ምን ያክል ከባህላዊው እውቀት የተፋቱ እንደመጡ የሚያሳይ ነው።  

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

Blog at WordPress.com.

Up ↑

%d bloggers like this: